ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቫይረሱን ለመከላከል የቤት ለቤት አሰሳ እየተካሄደ ነው

አሶሳ ግንቦት 03 / 2012( ኢዜአ) - በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል የቤት ለቤት አሰሳ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ 

በክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የጤና ቢሮው ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዋጮ ዋቡልቾ እንደገለጹት የቤት ለቤት አሰሳው የጤና ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃኞችን በማካተት በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች እየተመራ ቀጥሏል።

በአሰሳው የኮሮና ቫይረስ ላይ ያተኮረ የሰውነት ሙቀትን መለካትን ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡ 

" እስካሁን በክልሉ ከ90 ሺህ በላይ አባወራዎች እና እማወራዎችን ቤት ጎብኝቷል "ብለዋል፡፡ 

በጉብኝቱ ወቅት የሰውነት ሙቀታቸው ከመደበኛው በላይ ሆኖ የተገኙ 51 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ለሚሰሩ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ ኃይል ለተጨማሪ ምርመራ መላካቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገላጻ ከዚህ ስራ በተጓዳኝ  ከ231 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ስለቫይረሱ መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶች ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

የመከላከሉ ስራ በቀጣይም በተለይም ክልሉ ከአጎራባች ሱዳን ጋር የሚዋሰንባቸው አሶሳ ዞን ወረዳዎች ዋነኘ ትኩረት ተደርጎ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቫይረሱን  አስተቀድሞ ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ጨምሮ ሌሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን በመተግበር የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ የወረዳ ሁለት ነዋሪ ወይዘሮ ዓለም አብርሃ በሰጡት አስተያየት ሁሉንም ቤተሰቦቻው አስገዳጅ ጉዳይ ከሌለ በስተቀር ከመኖሪያ ቤት እንደማይወጡ ተናግረዋል።

በቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ ዳሰሳው የመጡ ባለሙያዎች የቤተሰቦቻቸውን የሰውነት ሙቀት መለካትን ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎችን እንዳደረጉም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም