ቀጥታ፡

አዋጁን በመተላለፍ ድግስ ያዘጋጁ ግለሰቦች ተቀጡ

አክሱም ግንቦት 3/2012( ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ድንጋጌ በመተላለፍ ድግስ ያዘጋጁ ግለሰቦች በገንዘብ እና እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ የጸጥታና መረጃ ሴክሬታሪያት አስተባባሪ አቶ ይሳቅ ገብረጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት በግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው ለኮሮና ቫይረስ  መስፋፋት ምክንያት የሆኑ የሰዎች መሰባሰብ  የሚከለክለውን የአዋጅ ድንጋጌ ጥሰው በመገኘታቸው ነው።

በዚህም በወረዳው የአውልዖ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  ነዋሪ የሆነው ግለሰብ ክልከላውን በመጣስ  ሰርግ ደግሶ በመገኘቱ የወረዳው ፍርድ ቤት 15 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል።

ሆኖም ግለሰቡ   ገንዘብ የለኝም በማለቱ   በአስር ወር ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑን  የሴክሬታሪያቱ  አስተባባሪ አስታውቀዋል።

ከዚህም ሌላ  በወረዳው የዱራ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ  የማህበር ድግስ አዘጋጅቶ በመገኘቱ ፍርድ ቤቱ በ15ሺህ ብር እንዲቀጣ የወሰነበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የድግሱ  ታዳሚ የነበሩ  16  ሰዎች ደግሞ  እያንዳንዳቸው በ500 ብር  መቀጣታቸውም አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በዝግጅት ላይ የነበሩ 112 ሰርጎች ደግሞ  እንዲቋረጡ መደረጉንም  አስተባባሪው አስረድተዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የህግ ባለሙያ አቶ ሓጎስ በርሃነ  በሰጡት አስተያየት " የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ሊታወቅ ይገባል "ብለዋል።

ህግ መከበር እንዳለበትና አዋጁን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦች ላይም  እየተወሰደ ያለው እርምጃ  ተገቢ  መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም