ቀጥታ፡

በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረናል - የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች

አክሱም 28/2010 በአክሱም ከተማ በተደጋጋሚ በሚከሰት የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት የባንክ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በከተማው ካለፈው ሰኔ 25 ቀን ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ከባንኮች ገንዘብ ማውጣትም ሆነ ማስገባት አለመቻላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ ካሳ በየነ እንዳለው በአገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያት ለመመረቂያ ዝግጅት ከቤተሰብ የተላከበትን ገንዘብ ማውጣት አልቻለም። የሚመለከተው አካል ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባም ገልጿል፡፡ የትግራይ ማእከላዊ ዞን የናዕዴር ዓዴት ወረዳ የንብረትና ግዥ አስተዳደር ባለሙያ አቶ ፍፁም ብርሃነ በበኩላቸው በየእለቱ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም በከተማው በተለይ ከሰኔ 25 ቀን ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ገንዘብ ከባንክ ለማውጣትም ሆነ ለማስገባት መቸገራቸውን ተናግረዋል። ሰኔ ወር የመንግስት መስሪያ ቤቶች የበጀት መዝጊያ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወራረድበትና የሂሳብ ዝውውር የሚፈጸምበት በመሆኑ የሚመለከተው አካል  አገልግሎት እንዲጀምር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት በሚፈልጉት ጊዜ የባንክ አገልግሎት ማግኘት አልቻልኩም ያሉት ደግሞ  የአክሱም ከተማ ነዋሪ መምህር ጎሹ ተስፋይ ናቸው። የወር ደሞዝ ማውጣት ባለመቻላቸው በገንዘብ እጥረት ለተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የንግስተ ሳባ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮውሃንስ ፋንታሁን በበኩላቸው፣ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ምክንያት ደንበኞቻቸው እየተጉላሉ መሆኑን ተናግረዋል። ባንኩም ስራውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻለም ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት የባንኩ ደንበኞች ከፍተኛ ቅሬታ እያሳሙ መሆናቸውንና የኢትዮ- ቴሌኮም ተቋም ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን ለመፍታት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮ- ቴሌኮም የሰሜን ዲስትሪክት ማስተባበሪያ የኔትወርክ አክሰስ እና የኢንተርኔት ቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋይ ወልደጊዮርጊስ ስለችግሩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የኢንተርኔት አገልግሎቱ የተቋረጠው ወደ ከተማው የተዘረጋው የኢንተርኔት ፋይበር ዓዲግራት ከተማ አከባቢ ብልሽት በማጋጠሙ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፋይበር ገመዱ የተበላሸበት ስፍራ ገደላማ በመሆኑ ምክንያት ለጥገና ጊዜ መውሰዱን  ያመለከቱት ኃላፊው አሁን ግን ጥገናው በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ አገልግሎት እንደሚጀምር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም