ቀጥታ፡

በኮቪድ-19 ላይ የሚመራመሩ ተቋማት መደበኛ ተልዕኳቸውንም መዘንጋት እንደሌለባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት  3/2012  (ኢዜአ) የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮቪድ-19 ምርምር ሲያካሂዱ መደበኛ ተልዕኳቸውንም መዘንጋት እንደሌለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከ52 የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ጥናት እንዲያደርጉ የኮቪድ-19 የጥናትና ምርምር ግብረ ኃይል መቋቋሙ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም እያስጨነቀ ያለውን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተቋማት በ14 የምርምር ይዘቶች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ይገኛል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወቅር ካሱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አደገኛነቱ በዓለም ጤና ድርጅት ስለተረጋገጠ ቅድሚያ ተሰጥቶታል ብለዋል።

በኢትዮጵያም የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመቆጣርና ለመከላከል የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወረርሽኙን በመከላከል ላይ አንዲያተኩሩ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

ኮቪድ-19 ካለፈ በኋላም ተቋማቱ  በወረርሽኙ ዙሪያ እየተመራመሩ ስለማይቀጥሉ በተጓዳኝ መደበኛ ስራቸውን ማከናውን አለባቸው ብለዋል ፕሮፌሰር አፈወርቅ።

በመሆኑም ተቋማቱ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት በሌሎች የጤና፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ከባቢያዊና ሳይንሳዊ ዘርፎች መዘናጋት የለባቸውም ብለዋል።

ሁሉም ተቋማት በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ተወስነው ምርምር የሚያደርጉ ከሆነ በቀጣይ ሌላ ሀገራዊ ርብርብ የሚጠይቅ አደጋ ቢከሰት ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀደምት የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዳሏት የገለጹት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የቴክኖሎጂ፣ የግብዓትና የሰው  ሃይል አደረጃጀት ግን የላቸውም ብለዋል።

በመሆኑም ኮቪድ-19 ያልታሰቡ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ተቋማት ዝግጁ ሆነው አንዲጠብቁ ትምህርት ሰጥቷል፤ ከዚህ በመማር ተቋማቱን ማደርጀትና ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ዙሪያ ጥናት ቢደረግባቸው ወረርሽኙን ለመከላከል ይበጃሉ ተብለው የተመረጡ 14 የምርምር ይዘቶች የተቋማቱን መደበኛ ተልዕኮ በማይጎዳ መንገድ የሚከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ ስርጭቱን እያስፋፋ መጥቶ አሁን ላይ ከ4 ሚሊዮን 100 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህመም ዳርጓል።

ከ282 ሺህ በላይ የዓለም ህዝቦችም በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን እንዳጡ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨረሲቲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም