በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማጭበርበር እና ዘረፋ ወንጀል ከሸፈ - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማጭበርበር እና ዘረፋ ወንጀል ከሸፈ
ግንቦት 2/2012 ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ረጅም ጊዜ በመውሰድ በተለያየ መንገድ ክትትል ሲያደርግበት የነበረው እና በጉዳዩም ላይ በቂ መረጃ ሲያሰባስብበት የቆየው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትን በመጠቀም 110 ሚልዮን ዶላር የማጭበርበር እና የዘረፋ የወንጀል ሙከራ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን አስታወቀ።
አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በላከው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ ነዋሪነቱ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በሆነው ኒል ቻርለስ የተባለ ግለስብ ስም በባንክ የተቀመጠ 110 ሚልዮን ዶላርን የባንክ ሒሳብ ባለቤቱ እንዳዘዘ አስመስለው አዲስ አበባ ከተማ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ተብሎ ከሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማውጣት የተለያዩ የማጭበርበር ስልቶችን ሲያቀናጁ እንደነበር አስታውቋል።
ይሁንና ሕገ ወጥ የገንዘብ ማዘዋወር እና ዘረፋ ወንጀሉ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ክትትል ስር የነበረ በመሆኑ፣ ግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በመጀመሪያ ዙር 60 ሚልዮን 9 መቶ 90 ሺህ 9 መቶ 39 ብር ከተጠቀሰው ባንክ አውጥተው በማዳበሪያ ጭነው ባዘጋጁት ተሽከርካሪ ሊወስዱ ሲሉ ቀድሞም በጥብቅ ክትትል ስር ስለነበሩ እዚያው ባንክ ውስጥ እያሉ በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብሏል።
ወንጀሉን በማቀነባበር ከሚታወቁት መካከል አድይሚ አድርሚ አብዱልራፊ የተባለ ናይጄሪያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ሸገር እንግዳ ማረፊያ በቀን 450 ብር እየከፈለ ከአንድ ዓመት በላይ በመቀመጥ ተልእኮውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሲያካሂድ በነበረው ክትትል አረጋግጧል።
ግለሰቡ ተልእኮውን ለማስፈጸም ዓለም አቀፍ ኤቲም ካርድ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ገንዘቡንም ከአሜሪካዊው ኒል ቻርለስ የባንክ ሒሳብ ቁጥር በቀላሉ እንደ ባለቤት ሆኖ ለማውጣት ያመቸው ዘንድ በኢትዮጵያ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን የሳይበር እና የአይቲ ባለሞያዎችን እንዲሁም ተያያዥ ሙያ ያላቸውን ግለሰቦች በመለየት እና በማጥናት የጥቅም ተጋሪ በማድረግ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ታውቋል።
በዚህ ወንጀል ለጊዜው አንድ ናይጄሪያዊ እና አምስት ኢትዮጵውያን በድምሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪዎችም እንዲያዙ ለማድረግ ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
ዓለም አቀፍ ገንዘብ የማስተላለፍ እና የመዝረፍ ወንጀሉን ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል መረጃ ተደግፎ በጥብቅ ሙያዊ ዲሲፒሊን ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ድረስ እየተከታተለ እና ተገቢውን አመራር እየሰጠ ውጤታማ እንዲሆን ማድረጉንም ጨምሮ ገልጿል።
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአገር ደህንነት እና በሕዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወንጀሎችንና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በማክሸፍ የሕዝብንና የአገርን ደህንነት እያስጠበቀ እንደሆነ በተከታታይ ካካሔዳቸው ኦፕሬሽኖች በመነሣት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ኅብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ ኦፕሬሽን የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ላደረጉት ትብብር አገልግሎቱ ምስጋና ማቅረቡን ኢብኮ ዘግቧል።