የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
ጎንደር፣ ግንቦት 02/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ድጋፍ በአማራ ክልል ለተቋቋሙ ሦስት የኮሮና ቫይረስ ሕክምና መስጫ ማዕከላት ከአንድ ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
ማኅበሩ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በደባርቅና በመተማ ከተሞች ለተቋቋሙት የኮሮና በሽታ ሕክምና መስጫ ማዕከላት ትናንት ድጋፉን አስረክቧል፡፡
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት በሽታው እየከፋ ቢሄድ ታማሚዎችን በሆስፒታሎቹ የተሟላ ሕክምና እንዲያገኙ በማሰብ የተደረገ ድጋፍ ነው።
ከድጋፉም ውስጥ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስና አንሶላ እንዲሁም ለንጽሕና መጠበቂያ የሚውሉ ፈሳሽና ደረቅ ሣሙናዎች ይገኙበታል።
ማኅበሩ በቀጣይም በምዕራብና ምሥራቅ አማራ በሚገኙ ዞኖች ለተቋቋሙ የኮሮና ቫይረስ የሕክምና መስጫ ማዕከላት ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ኃላፊው ገልጸዋል።
የጎንደር ዩንቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራአስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው ድጋፉ ሆስፒታሉ ያቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ሕክምና መስጫ ማዕከል ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያግዘው መሆኑን ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በቅርቡ በጀመረው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊ፣ ሰሜንና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የሚላኩለትን ናሙናዎች እየመረመረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ድጋፉ የሆስፒታሉን አቅም ከማጠናከር ባለፈ በሽታውን ለመቆጣጠር እንደዚህ ዓይነት የጋራ መደጋገፍ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ሥዩም ናቸው።
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ደምሴ በከተማው ለተቋቋመው የሕክምና መስጫ ማዕከል ማኅበሩ ከ100 በላይ ፍራሾች እንዲሁም አንሶላ፣ ብርድ ልብስና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መድረጉን በመግለጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ማኅበሩ ባለፈው ወር በከተማው ለተቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው "ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ ማኅበሩ ያደረገው ድጋፍ የሚያበረታታ ነው" ብለዋል፡፡
በሌላም በኩል ማኅበሩ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ወደ ቀያቸው ከተመሰሉ በኋላ በበሽታው ሳቢያ በቤት ውስጥ ለሆኑ 25 አቅም ደካሞች የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
በማኅበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ "ማኅበሩ ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ በማዕከላዊ፣ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለበሽታው ግንዛቤ ሰጥቷል" ብለዋል።