ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር የኮሮና መከላከያ ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፣ ግንቦት 2/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር 300 ሺህ ብር የሚገመት የኮሮና መከላከያ አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ ለደቡብ ክልል ጤና ቢሮው አስረከበ።

ማህበሩ ድጋፉን የሰጠው  አለም አቀፉን የአዋላጅ ነርሶች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።

የድጋፍ ርክክቡ ትናንት በተካሄደበት ወቅት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ አካሉ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ክስተትን ተከትሎ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ቀንሷል።

ይህንን ለማስተካከል መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዚህ በተጓዳኝ  አዋላጅ ነርሶች ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ለማገዝ ማህበሩ ለሁሉም ክልሎች አንድ ሚሊዮን 600ሺህ የሚገመት አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ 300ሺህ ብር የሚገመተው ለደቡብ ክልል አዋላጅ ነርሶች  አገልግሎት እንዲሆን አስረክበዋል።

ይህም አዋላጅ ነርሶች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ መከላከል እንዲችሉ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት የሚጠቀሙባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሁሉም ከቤት መውጣት እንደሌለበት እየተገለጸ መሆኑን ጠቁመው ነፍሰጡር እናትና አዋላጅ ነርሶችን ግን ስለማይቻል ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ አገልግሎቱን መስጠት የግድ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ 17 ሺህ አዋላጅ ነርሶች እንደሚገኙና  ይህም በቂ እንዳልሆነ ተመላክቷል።

መንግስት የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥር በማሳደግ በቤት ውስጥ የሚወልዱና ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ መስራት እንዳለበትም አቶ ዘነበ ገልፀዋል።

የደቡብ ክልል አዋላጅ ነርሶች ማህበር ጸሀፊ ሲስተር ቅድስት እሸቱ በበኩላቸው ኮሮናን በመስጋት እናቶች ወደ ጤና ተቋም  መጥተው ለመውለድ እንደሚፈሩ ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ በአዋላጆችም ዘንድ ስጋት አሳድሮ እንደነበር ገልጸው  "ለጥንቃቄ የሚያስፈልጉ አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ችግሩን ያቃልለዋል "ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም