ቀጥታ፡

ዋግ ልማት ማህበር የህክምና እና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

ባህርዳር፣ ሚያዚያ 02/09/2012( ኢዜአ ) ዋግ ልማት ማህበር ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ ከ895 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ህክምናና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ድጋፍ አደረገ፡፡ 

የልማት ማህበሩ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ባምላኩ አበበ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የማህበሩ አባላት እና ደጋፊዎች ድጋፍ ሲያሰባስብ  ቆይቷል።

ድጋፉም ከነዚሁ አባላትና ደጋፊዎች እንደተሰበሰበ አመልከተው ይህም 700 ካርቶን የንፅህና መጠበቂያ ሳሙና፣ የሃኪሞች አልባሳት፣  መድኃኒት እና የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ቁሳቁሶቹን ለብሄረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ትናንት ማስረከባቸውና  በቀጣይም ማህበሩ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልግቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ እርዳታ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የኮሮና  መከላከል ሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ተስፋየ ገብሬ በበኩላቸው ቫይረሱ ቀድሞ ለመከላከል ልማት ማህበሩ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ለሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

"በልማት ማህበሩ የተደረገላቸው ድጋፎች በሰቆጣ ከተማ ለተቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል ያለበትን የግብአት እጥረት የሚቀርፍ ነው "ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል አባል አቶ ሞገስ መርካ ናቸው፡፡

ለተደረገላቸው ድጋፍም  ዋግ ልማት ማህበርን አመስግነዋል፡፡

በቀጣይም በብሄረሰብ አስተዳደር ደረጃ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማሽን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም