ተቋማቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በቅድሚያ መከላከልን መሠረት ባደረጉ ጥናቶች ላይ መሰማራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በቅድሚያ መከላከልን መሠረት ባደረጉ ጥናቶች ላይ መሰማራት አለባቸው
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በቅድሚያ መከላከልን መሠረት ባደረጉ የምርምር ይዘቶች ላይ እንዲሰማሩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ በትክክል አለመተግበር በጤና፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች ጉዳት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ ከምርምርና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር "ዘርፈ ብዙ የኮቪድ 19 ምርምር የትኩረት ይዘቶች - በኢትዮጵያ የምርምር ግኝት" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዛሬ የቪዲዮ ኮንፍረንስ አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የምርምር ሥራዎችን የሚያካሂድ የኮቪድ-19 የጥናትና ምርምር ግብረ ኃይል መቋቋሙ ይታወቃል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ ከተቋማቱ በተውጣጡ ምሁራን በሽታውን ለመቆጣጠር ጥናት ቢደረግባቸው ይበጃሉ የተባሉ አማራጮች ተለይተዋል።
ተቋማቱ በኢትዮጵያ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳና ስዊዘርላንድ በሚገኙ 283 ምሁራን በተለዩ 14 መስኮች ላይ ጥናት ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት አገሮች ኮቪድ-19ን ለመከላከል ጥናት ቢያደርጉባቸው የተሻሉ አማራጮች ናቸው ብለው ያቀረባቸውን 41 የትኩረት ይዘቶችና የአፍሪካ የሳይንስ አካዳሚዎች ኅብረት ምክረ ሃሳብ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መለየታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የተለዩት ወረርሽኙን መቆጣጠር፣ መከላከል፤ ህሙማን እንክብካቤና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
በኮንፍረንሱ ላይ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የግብረ ኃይሉ አባል ዶክተር ጌትነት ይማም በቅድሚያ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና ሌሎች መከላከልን መሠረት ባደረጉ ይዘቶች ላይ ጥናት ማካሄድ ይገባል ባይ ናቸው።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከቦታ ቦታ የሚያሳየው ባህርይ ተለዋዋጭነት፤ ከእንስሳት ወደ ሰው ወይም ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፍበት ሂደት እንዲሁም በከባቢ አየር ውስጥ ያለው ቆይታና የስርጭት ሁኔታው በትክክል እንደማይታወቅ አመልክተዋል።
የኅብረተሰብ ጤናና ተዛማች በሽታዎች ተመራማሪ ፕሮፌሰር የማነ ብርሃን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ በትክክል የማይተገበር ከሆነ በአገር ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ''ይከፋል" በማለት ጥንቃቄ እንዲደረግበት ይመክራሉ።
በመሆኑም የምርምር ተቋማት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለመከላከል በዓዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ከአተገባበር ጀምሮ መፈተሽ አለባቸው ብለዋል።
ወረርሽኙ በጤና፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ትብብር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል የሚቻለው በፉክክር ሳይሆን፤ በትብብር ነው ይላሉ።
ተቋማቱ በፉክክርና በትብብር መስራት ጤናማ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን በትብብር ብቻ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
መንግሥት በጥናትና ምርምር ዘርፍ የተሰማሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አረጋግጠውላቸዋል።