ቀጥታ፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ቢቀሰቀስም የቡና ወጪ ንግድ እድገት አሳይቷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2012( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ(ኮቪድ-19) በኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ላይ የጎላ ተጽዕኖ አለማሳደሩን የቡና ላኪዎች ማህበር ገለጸ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ከ561 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። 
 

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮቪድ-19 በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ቢያሳድርም፤ ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ ያልተጠበቀ እድገት አሳይቷል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 194 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 561 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስረድተዋል።

በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው ወረርሽኝ በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ያሳደረው ጫና በቡና ወጪ ንግድ ላይ የጎላ ተጽዕኖ አለማሳደሩን የገለጹት ዋና ሥራ አከኪያጁ፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት ወራት የገቢ ቅናሽ አልታየም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ኮፊ አረቢካን ዋና ዋና ተቀባይ ለሆኑ ጀርመን፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና አሜሪካ እያቀረበች መሆኗንም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የአገሪቱን የቡና ወጪ ንግድ 20 በመቶ የሚሸፍነው ልዩ ቡና በዓለም ላይ ካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ በቀጣዮቹ ወራት በዓለም እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚያስከትለውን ሁኔታ መተንበይ እንደማይቻል ያስረዱት አቶ ግዛት፤በበሽታው ምክንያት የሚጣሉ ክልከላዎች ከቀጠሉ በንግዱ ላይ ብቻ ሳይሆን ምርታማነቱ ላይም ጫና ያሳድራል ብለዋል።

በመሆኑም በአቅርቦት ሰንሰለት፣ በትራንስፖርትና ሌሎች ላይ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም