በደቡብ ወሎ ዞን በደረሰ የተሸከርካር አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በደረሰ የተሸከርካር አደጋ የስምንት ሰዎች ህይወት አለፈ

ደሴ፤ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በለጋአምቦ ወረዳ በደረሰ የተሸከርካር አደጋ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ በስድስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገለጸ።
በዞኑ የለጋምቦ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የመንገድ ደህንነት ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር መሃመድ አደም እንደገለጹት፤ ዛሬ ረፋዱ ላይ በደረሰው የትራፊክ አደጋ አሽከርካሪውን ጨምሮ የስምንት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
አደጋው የደረሰው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አማ 23330 የህዝብ ማመላለሻ አይሱዙ ከከላላ ከተማ ተነስቶ ወደ ደሴ ከተማ በመጓዝ ላይ እንዳለ ለጋምቦ ወረዳ 029 ቀበሌ ሲደርስ በግምት ከ150 ሜትር በላይ ገደል ውስጥ በመግባቱ ነው ።
በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በስድስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በመድረሱ ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች በአቀስታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ ናቸው ።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም አሽከርካሪው እንቅልፍ ሳይወስደው እንዳልቀረ ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።
የሟቾችን አስክሬን በመለየት ወደ የቤተሰቦቻቸው የመላክ ስራ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው አሽከርካሪዎች የሰው ህይወት የአገር ሃብት ጭምር መሆኑን በመገንዘብ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ ምክር ለግሰዋል።