ቀጥታ፡

ሠራተኞቹ የኮሮናን ወረርሽን ለመከላከል ከ386 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አስረከቡ

 አዲስ አበባ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር የኮሮና ወረርሽኝን የሚከላከልበት ከ386 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አበረከቱ።

የፕሮጀክቱ  ሥራ አስኪያጅ አቶ መብራቱ  ተሾመ  በድጋፉ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ  እንደተናገሩት ድጋፉ ለድርጅቱ የተደረገው መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ባቀረበው ጥሪ መሠረት ነው፡፡

ሠራተኞቹ  አገራዊውን ጥሪ በመቀበል ያሰባሰቡትን ገንዘብ  ለድርጅቱ ለመስጠት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሠራተኞቹ ለድርጅቱ ድጋፉን በማድረጋቸው የህሊና እርካታ እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል።

የጌርጌሴኖ የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር  መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አየለ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ሠራተኞቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ድጋፉንም  ''በአስቸጋሪ  ወቅት የደረሰ''ብለውታል።

ሌሎችም ተቋማት  የሠራተኞቹን አርአያነት በመከተል ድጋፍ እንዲያበረክቱላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ተወካዮች አቶ ግዛቸው ደሳለኝና አቶ ተስፋዬ ጥላሁን በበኩላቸው ሠራተኞቹ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ''የማዕድ ማጋራት'' ጥሪ በመቀበል በራሳቸው ፍላጎት ድጋፉን ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከወገን በተለይም በድርጅቱ ከሚረዱ ሰዎች ተጋግዞና ተካፍሎ በመብላት መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በደቡብ ክልል ኮይሻ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ የተሰማራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም