ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ያለውን የሰዎች ዝውውር ለመግታት ጥረት እየተደረገ ነው

ጋምቤላ ኢዜአ ግንቦት 1 / 2012 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች ያለውን የሰዎች ዝውውርና የስደተኞች እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የስደተኞች እንቅስቃሴ አለ ።

ይህም በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበር ላይ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ ለቫይረሱ ስርጭት ስጋት እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመከላከል ከሚመለከታቸው የጸጥታ ኃይሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የስደተኞችን ያልተገደበ እንቅስቃሴ ለመግታት ከስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል ዶክተር ኡጁሉ ኡጁሉ በበኩላቸው ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚወጡና የሚገቡ ሰዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል ።

የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ቢዘጋጁም ሰዎች ከኬላዎች ውጪ ስለሚገቡና ስለሚወጡ ወደ ለይቶ ማቆያ ቦታዎች ማስገባት እንዳልተቻለ ጠቁመው ይህም ክልሉ ለበሽታው  ይጋለጣል የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልፀዋል ።

በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት እንደሚሉት በድንበር አካባቢ ያለውን የሰዎች ዝውውር ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ድንበሩ ሰፊና ህዝቡም ተመሳሰይ በመሆኑ የቁጥጥር ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል ።

በአካባቢው  ባደረጉት የመስክ ምልከታም ክፍተቶች እንዳሉ ማረጋገጥ መቻላቸውን ነው የገለጹት ።

ህብረተሰቡን በማሳተፍ ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን በመቆጣጠሩ ሒደት የሚታዩትን ክፍተቶች  የማስተካከል ስራዎች እንደሚከናወኑ ነው ሜጄር ጀኔራሉ የተናገሩት።

የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉና ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በጠረፋማ አካባቢዎች ተዘዋውረው ምልከታ አካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም