በኮሮና ቫይረስ ለችግር የሚጋለጡ ወገኖችን የሚረዱ ከ1ሺ በላይ አደረጃጀቶች ተዋቀሩ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና ቫይረስ ለችግር የሚጋለጡ ወገኖችን የሚረዱ ከ1ሺ በላይ አደረጃጀቶች ተዋቀሩ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1 /2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ይበልጥ ለችግር የሚያጋልጣቸውን ወገኖች የሚረዱ ከ1ሺ በላይ አደረጃጀቶች መዋቀራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር አስታወቀ።
አስተዳደሩ በኮሮና ወረርሽኝ ለማህበራዊ ችግር የሚጋለጡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ለመደገፍ ከ1ሺ 3መቶ በላይ አደረጃጀቶች በማዋቀር ከመንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የሚሰበስበውን ሀብት አቀናጅቶ የሚመራ ግብረ ኃይል በማቋቋም ነው ስራውን የጀመረው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ አስተዳደሩ ለማህበራዊ ችግር የሚጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ ሃብት እያሰባሰበ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ተቋማት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ህብረተሰቡ በአካባቢያቸው የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖችና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ በጎ ተግባር ከተሰማሩት በርካታ ድርጅቶች መካከል 514ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉን የነገረን ኤች ኤስ ቲ ኮንሰልታንስ ነው፡፡
ድርጅቱን በመወከል ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ቶማስ ሙሉጌታ ከአሁኑ ድጋፍ በተጨማሪ በተቋማቸው አካባቢና በሚሰሩበት ቦታ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የምግብ ቁሳቁሶችን ለግሷል፡፡
የዶች በን ድርጅት ተወካይ አቶ ሳሙኤል ብሩ በበኩላቸው እንደ አገር የተላለፈውን ወገናዊ ጥሪ በመቀበል ድርጅታቸው 200 መቶ ሺ ብር ደግፏል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪም ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል በቀጣይም መንግሥት ለሚያቀርበው ወገናዊ ጥሪ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛሆኖ ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ መንደርን ማዕከል ያደረገ 1ሺ357 አደረጃጀቶች መዋቀራቸውን ያስታወቁት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የኮሙዩኒኬሽንና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ነስረዲን መሐመድ ናቸው፡፡
ከህብረተሰቡ የተውጣጡት አደረጃጀቶች ካከማቹት የምግብ ቁሳቁሶች ብዙ የማይቆዩትን ምግቦች በከተማ ደረጃ ለተዋቀረው የምግብ ባንክ ማስረከባቸውን አስረድተዋል፡፡
በአብነትም ለፋሲካ በዓልና በሮመዳን ጾም ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የድጋፍ ስራውን የበጎ አድራጎት ተቋማትም እየተሳተፉበት መሆኑን ጠቁመው በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ከመንግስት መዋቅር ጋር በመደራጀት ስለ ኮቪድ 19 ግንዛቤ እየሰጡ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ በቀጣይ በትራንስፖርት ዘርፉና የሰዎች እንቅስቀሴ በሚበዛባቸው የግብይት ቦታዎች ላይ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራትይከናወናል ብለዋል።፡
በአዲስ አበባ ከተማ 400ሺ የሚጠጉ ድጋፍ የሚሹ አባወራዎች መለየታቸውን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡