ዩኒቨርሲቲዎቹ በመተማ ለይቶ ማቆያዎች ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎቹ በመተማ ለይቶ ማቆያዎች ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ
መተማ ኢዜአ 01/09/2012 የባህር ዳርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች በምዕራብ ጎንደር ዞን በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎች ለማህበራዊ ችግር እንዳይጋለጡ የምግብ እህልና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።
የዞኑ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል ፀሃፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ከዩኒቨርሲቲዎች የተላከውን ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ በማቆያ ቦታዎች ለነበረው የምግብና ሌሎች የግብዓት እጥረቶች ጊዜያዊ መፍትሄ ይሰጣል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁለት የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን ጨምሮ 200 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 15 ኩንታል የጤፍ ዱቄት፣ 10 ኩንታል ፓስታ፣10 ኩንታል ሩዝ፣ 4 ኩንታል ነጭ ሽንኩርትና 50 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና መስጠቱን ገልፀዋል።
የዩኒቨርስቲው ድጋፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲም 50 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ አምስት ኩንታል ሽሮ እና ሶስት ኩንታል በርበሬ ድጋፍ ማድረጉን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች ያደረጉት ድጋፍ ከ450 ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለው ገልጸው ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ሆኑ ተቋማት የዞኑን ለኮሮና ቫይረስ የተጋላጭነት ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባትም የድጋፍና የጥንቃቄ ስራዎችን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በዞኑ ውስጥ በተቋቋሙ አምስት የለይቶ ማቆያ ቦታዎች 327 ዜጎች እንደሚገኙ አመለክተው፤ ከዚህ በፊት 675 ዜጎች በማቆያ አልፈው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን አመላክተዋል፡፡