ቀጥታ፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ኮሮና ለመከላከል የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለፀ

ጋምቤላ ኢዜአ ግንቦት 01 ቀን 2012 ዓም.የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ የአጋርነት ሚናውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገለፀ ። 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልፇል ።

ዩኒቨርሲቲው  የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ማምረት ጀምሯል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በአካባቢው ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

በተለይም ዩኒቨርሲቲውን ለለይቶ ማቆያና ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ ህንፃዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ቫይረሱን ለመከላከል የሚስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በአካባቢው የነበረውን የንጽህና መጠበያ እጥረት ለማቃለልና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ ሳኒታይዘር በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቅርቡም ከሶስት ሺህ ሊትር በላይ ሳኒታይዘር ለማህበረሰቡ ያሰራጫል ብለዋል።

በተጨማሪ ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች የዩኒቨርሲቲው መምህራን ለማሰማራት መታቀዱን ፕሬዘዳንቱ ገልፀዋል ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋሉዋክ የዩኒቨርሲቲው የሳኒታይዘር ማምረቻ ማዕከል በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት የኮሮና ቫይረስን ለመከለካል በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲው የአጋርነት ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በተለይም ከለይቶ ማቆያና ከህክምና አገልግሎት መስጫ ማእከላት ማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው እየተመረተ ያለው የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ቀደም ሲል በክልሉ ሲታይ የነበረውን የንጽህና መጠበቂያ እጥረት ያቃልላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም