ቀጥታ፡

ህግ የማስከበር ስራው የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - የህግ ባለሙያዎች

መቱ (ኢዜአ) ሚያዝያ 30/2012 - በየጊዜው እየጨመረ ያለው የኮሮና ቫይረስ በህዝብና በአገር ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ህግ የማስከበር ስራው የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በመቱ ከተማ የሚገኙ የህግ ባለሙያዎች አስገነዘቡ::

የዓለም ሁሉ ስጋት የሆነውን የኮረና ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲያግዝ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ በተግባር አውሏል።

ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ መመሪያዎች ቫይረሱን መከላከል በሚያስችል ሁኔታ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ እየተፈጸመ አይደለም የሚል ቅሬታ እየተነሳ ነው ።

የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ታዲያ የመመሪያዎቹ ተፈጻሚነት ላይ የሚታየው መንጠባጠብ አገሪቷን ከባድ ዋጋ እንዳያስከትል ከወዲሁ ሊሰራበት ይገባል።

በተለይም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ በማክበርና በማስከበር ረገድ ውስንነቶች ይታያሉ ሲሉ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ ።

የመቱ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ዓይናለም በዛብህ በሰጡት አስተያየት "ህብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የወጡትን ህጎች በሚፈለገው ልክ እያከበረ አይደለም "።

በተለይም በመቱ ከተማና አካባቢው አሁንም ድረስ በመጠጋጋት መገበያየትና በአንድ ቦታ የመሰባሰብ ሁኔታ እንዳለ መቀጠሉን መታዘባቸውን ተናግረዋል::

"ህብረተሰቡ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም በስልክ ጥሪዎች በየዕለቱ መልእክቶችን እያገኘ ነው" ያሉት አቶ ዓይናለም  የሚታየው መዘናጋት ግን የግንዛቤና የዕውቀት ችግር ሳይሆን "ቸልተኝነት በመሆኑ የሚመለከተው አካል የህግ ማስከበር ስራውን በተገቢው መልኩ ማከናወን አለበት" ብለዋል።

የመቱ ዩኒቨርስቲ በዚህ መስክ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጥናት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አክለዋል::

በመቱ ከተማ በግል ጥብቅና ስራ የተሰማሩት አቶ አሰፋ ጉርሙ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ውስጥ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ህግ በሚጥሱት ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሊጣል እንደሚገባ አውስተው  ለዚህም ህጉን ለማስከበር የቆሙ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል::

የህዝብን ጤና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለየ መልኩ ጥብቅ ቁጥጥር ይፈልጋል ያሉት ባለሙያው በአጥፊዎች ላይ ተገቢውንና አስተማሪ ቅጣት መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በዋናነት በማስተማር ላይ ብቻ ሳይሆን ቁጥጥርም ጭምር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ ጀማል አባሚልኪ የተባሉ የመቱ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

በተለይም በወጣቶች ዘንድ አካላዊ ንክኪ፣ መሰብሰብና ቡድናዊ ክንውኖች እስከ አሁንም እንዳልቀረ መታዘባቸውን ይናገራሉ።

የኢሉ አባቦር ዞን ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዞኑ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ተሰማ ኢተፋ በበኩላቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን ሙሉ ለሙሉ በማስከበሩ ረገድ ውስንነት እንዳለ አምነዋል።


በተለይም ህጉን የሚተላለፉ አካላትን በህግ ጥላ ስር ለማቆየት የማረሚያ ቤቶች አመቺ ያለመሆን ሌላ ችግር እንዳያስከትል በሚል ተግባራዊ ሳይደረግ ቢቆይም ሌሎች እርምጃዎች ግን እየተወሰዱ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

አሁን ግን በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የታራሚዎች ማቆያ ስፍራ ለቫይረሱ በማያጋልጥ መልኩ እየተዘጋጀ በመሆኑ ህግ የማስከበር ስራው በተገቢው ሁኔታ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም