ኮቪድ-19ን ለመከላከል ለድጋፍ ሰጭዎች፣ ለጤና እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ለመስጠት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19ን ለመከላከል ለድጋፍ ሰጭዎች፣ ለጤና እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ለመስጠት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) ኮቪድ-19ን ለመከለካል ድጋፍ ለሚሰጡ፣ የጤና እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ::
የመግባቢያ ሥምምነቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ ፈርመውታል።
በሥምምነቱ መሰረት የኮሮናቫይረስ ለመከላከል በተለያዩ የጤና ተቋማት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የህይወት መድን ሽፋን ይደረግላቸዋል።
በለይቶ ማቆያ፣ በኳራንቲን፣ በላብራቶሪ ምርመራ ማዕከል፣ በፈጥኖ ምላሽ ቡድን፣ በድንገተኛና በሌሎች ክፍል የሚሰሩ ባለሙያዎችን ይሸፍናል ተብሏል።
ጎን ለጎንም ጽዳቶች፣ የአንቡላን ሹፌሮችና ሌሎችም ፊት ለፊት የሚሰሩ ባለሙያዎች በዚሁ የህይወት መድን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት፤ መድኑ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ለፊት ለሚሰሩ ባለሙያዎች የሚቀርብ ነው።
ድጋፉም የአደጋና የህይወት መድን እንደሚያጠቃልል ገልጸው፤ ''የተደረሰውም ሥምምነት ድጋፉን እውን ለማድረግ ይረዳል ነው'' ያሉት።
ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ በበኩላቸው ድርጅታቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ ቆይቷል።
በዛሬውም ዕለት የዚሁ የድጋፍ አካል የሆነውን የህይወት መድን ሽፋን ለመስጠት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ድርጅቱ ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዶክተር ሊያም ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት ምስጋና አቅርበዋል።