ወቅታዊውን ችግር ለመሻገር "የሕገ መንግስት ትርጉም" የተሻለ አማራጭ ነው ... የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎችና ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ወቅታዊውን ችግር ለመሻገር "የሕገ መንግስት ትርጉም" የተሻለ አማራጭ ነው ... የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎችና ምሁራን
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2012 (ኢዜአ) አሁን ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመሻገር "የሕገ መንግስት ትርጉም" የተሻለ አማራጭ መሆኑን የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎችና ምሁራን ተናገሩ።
ዘንድሮ ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ ለማራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔም ትክክለኛና ወቅታዊ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስድስተኛውን ብሄራዊ ምርጫ ለማራዘም ከቀረቡት አራት አማራጮች መካከል "ሕገ መንግስት መተርጎም" በሚለው የመፍትሄ አማራጭ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም ውሳኔውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እንዲመለከተው ተልኳል።
ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ የተለያዩ የአገሪቷ የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ሕገ መንግስትን መተርጎም ከተባለው ውሳኔ ይልቅ የሽግግር መንግስት የተሻለ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሱማሌ ክልል የጎሳ መሪዎችና ምሁራን በምክር ቤቱ የተወሰነው ውሳኔ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ አስፈሪና አስጊ እየሆነ በመጣበት ወቅት "ምርጫው ይደረግና የሽግግር መንግስት ይመስረት" የሚሉ አካላት ለአገርና ህዝብ ሊያስቡ ይገባቸዋል ብለዋል።
የጎሳ መሪው ሃርጋንቲ ጀማል ባርጊች ከወረርሺኙ በላይ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ባለበት ወቅትና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ባለበት አጋጣሚ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት ዓለም አቀፉን የኮሮናቫይረስን ጨምሮ ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመውት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ባለበት ወቅት ማገዝ ሲገባ አፍራሽ ሆኖ መገኘት የሚሹ አካላትም እየተሳሳቱ መሆኑን ይናገራሉ።
በመሆኑም እሳቸው እንደ ጎሳ መሪና እንደ ሱማሌ ሕዝብ ተወካይ ምክር ቤቱ የደረሰበትን ውሳኔ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚሉ አካላት በአገሪቷ ውስጥ ምን ያክል ውስብስብ ችግር እንደሚፈጥር መረዳቱ እንደማያቅታቸውም እንገነዘባለን ብለዋል።
''ነገሩ ወደ 1983 ዓ.ም ለመመለስና ነገሮችን ከዜሮ ለመጀመር መሞከር ነው'' በማለት እሳቤው ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑን ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ያልሆኑ አማራጮችን የሚመሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ህዝቡ በፍጹም መስማት የለበትም ያሉት ደግሞ አቶ አብዱ መሓመድ ኡስማን ናቸው።
እሳቸውም እንደ አንድ የአገሪቷ ዜጋም ሆነ እንደ ሶማሌ ሕዝብ የምክር ቤቱ ውሳኔ የተሻለና የሚያዋጣ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜ ከኮቪድ 19 በላይ ለኢትዮጵያ አሳሳቢ ጉዳይ ባለመኖሩ ሌላው ጊዜውን ጠብቆ መከናወን የኖርበታል የሚሉት ደግሞ ዶክተር አብዲ መሓመድ ናቸው።
በቀደሙት ዘመናትም ከሌሎች ክልሎች በላይ ተጎጂ ሆኖ የቆየው የሱማሌ ክልል ከምርጫውም ቀድሞ ብዙ የሚያሳስቡ ነገሮች አሉት ብለዋል።
መሰል ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ቅድሚያ ለህዝብና ለአገር ደህንነት ነው የሚሰጠው ብለዋል የጎሳ መሪዎቹና ምሁራኑ።
ስለሆነም እሳቸውና የክልሉ ምሁራን ቀጣዩን ምርጫ ለማራዘም እየተሄደበት ያለው መንገድ ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ።
ሌሎች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የገነቡ አገራት እንኳ ምርጫና መሰል ህዝባዊ ስብስቦችን የሚጠይቁ ሁነቶችን እያራዘሙ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮቪድ 19 አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ ሚሊዮኖችን ታማሚ አድርጓል።
እስካሁን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከ 274 ሺህ 900 በላይ መሻገሩን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመለክታል።