ቀጥታ፡

ከኮሮናቫይረስ ጋር የመጀመሪያ ተፋላሚ የሆኑት የህክምና ባለሙያዎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ድንቅ አርበኝነት ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2012 (ኢዜአ) ''ቤተሰቦቻቸውን ትተው፤ ሕይወታቸውን አደጋ ውስጥ ከተው፤ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የመጀመሪያ ተፋላሚ የሆኑት የህክምና ባለሙያዎቻችን የሚከፍሉት መስዋዕትነት ሌላው ድንቅ አርበኝነት ነው'' ሲሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

በየዓመቱ ሚያዝያ 30 የሚታሰበውን የዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀንን በማስመልከት ፕሬዚዳንቷ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስቦ መዋል ከጀመረበት እ.አ.አ ከ1948 አንስቶ የሰዎችን ክብር፣ ጤናና ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም ለተቸገሩ የመድረስ እሳቤዎችን በጉልህ ሲያንጸባርቅ እና ሲተገብር መቆየቱን በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።

የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ እንቅስቃሴ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከችግር እና ከስቃይ የገላገለ፣ በሽታዎችን የፈወሰ፣ ለተንገላቱት የተረጋጋ ሕይወት የሰጠ ዓለም ዓቀፋዊ የጋራ መግባባት የተያዘበት ሰብዐዊ ተግባር መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፤ ''በዓለማችን ላይ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ ይህን የሠብዓዊነት መንፈስ እጅግ በተጠናከረ መንገድ እንድናድሠው ግድ የሚልበት ሁኔታ ላይ አድርሶናል'' ብለዋል።

የዘንድሮው የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን "ለጤና ባለሙያዎቻችን እጅ እንነሳለን፤ እናደንቃችኋለን" የሚለው መሪ ቃል እጅግ አግባብ የሆነ፤ ትክክለኛ መልዕክት መሆኑን ገልጸዋል።

''ቤተሰቦቻቸውን ትተው፣ ሕይወታቸውን አደጋ ውስጥ ከተው፣ ከወረርሽኙ ጋር የመጀመሪያ ተፋላሚ የሆኑት የህክምና ባለሙያዎቻችን የሚከፍሉት መስዋዕትነት ሌላው ድንቅ አርበኝነት ነው'' ብለዋል።

በ1927 ዓ.ም የተመሰረተው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለመከላከል የሚደረገውን አገራዊ ርብርብ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

''የገጠመንን ጠላት ለመከላከል ማህበረሰባዊ ንቃትና ተሳትፎን ማጠናከር ቁልፍ ተግባር ነው'' ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ፤ ''ኮቪድ-19 አንዳችን ለሌላችን በእጅጉ የምናስፈልግበትን ምክንያት እንዲሁም ፈተናዎቻችንን በተናጠል ሳይሆን በቅንጅት ድል መንሳት እንደምንችል ቁልጭ አድርጎ ያሣየን ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል'' ብለዋል።

''ተባብረንና ተሠባስበን የጋራ ክንዳችንን በማሳረፍ ራሳችንንም ሆነ አገራችንን ከወረርሽኙ እንታደግ'' ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ ከተሞች ቫይረሱን ለማምከን የኬሚካል ርጭት በማከናወን፣ ለህብረተሰቡ ድጋፍ የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት፣ የንፅህና መጠበቂያዎችን በማሰራጨት እና የማኅበሩ አምቡላንሶችን ለህብረተሰቡ አገልግሎት ዝግጁ በማድረግ ያሳየው ተነሳሽነት ሊቀጥል የሚገባው ድንቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ይፋ የተደረጉ በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ቀጣዮቹ ቀናትና ሳምንታት ከባድ ሊሆኑ እንደሚችል የሚያመላክት መሆኑን ገልጸው፤ ''አሁንም ማህበረሰቡ በመንግስትና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች በጥብቅ እንዲተገብር፤ ብሎም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች በምንፈልገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ቀንና ሌሊት መስራት የግድ ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በመላ አገሪቱ የዘረጋቸውን መዋቅሮች በመጠቀም ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት፣ የበጎ ፈቃደኝነት እና የመልካም ዜጋ ባህል እንዲሰፋ ማድረግ የሚጠበቅበት መሆኑን የበላይ ጠባቂዋ አስገንዝበዋል።

''ማህበሩ ቀበሌ ድረስ የሚገኘውን መዋቅሩን በመጠቀም ህብረተሰቡን ሊያነቃ፣ ሊያስተምር እንዲሁም የሚታይና የሚጨበጥ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ የጀመራቸውን ሥራዎች ማጠናከር ይኖርበታል'' ብለዋል።

በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎችን 'አለሁላችሁ ማለቱን መግፋት አለበት' ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም