ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል እና ዲላ ከተማ የቁሳቁስና ምግብ ድጋፍ ተደረገ

ሐረር፣ ዲላ ሚያዚያ 30/2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልልና ዲላ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ አልባሳት፣ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ።

በሐረሪ ክልል ድጋፉን ያደረገው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሲሆን ይህም ግምታቸው  ከ400 ሺህ ብር በላይ የሚሆን አልባሳትና ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ናቸው።

ድጋፉን በማኅበሩ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስፋው ሰንበቶ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት አቶ አስፋው እንዳሉት ማኅበሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

በተለይ ማኅበሩ  በክልሉ ከተቋቋመው ሀብት አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ ጋር በድጋፍ ሥራዎች ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

በማኅበሩ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 200 ፍራሽና ብርድ ልብስ፣ 100 ጥንድ አንሶላዎች፣ 100 የመሬት ምንጣፍና 120 ጋሎን ፈሳሽ ሣሙና እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ኦርዲን በድሪ ለተደረገው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፉ ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ለተቸገሩ ወገኖች ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን እገዛ  አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የሀብት አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማኅበር ያደረገው ድጋፍ በክልሉ ለተቋቋሙ የለይቶ ማቆያ፣ መከታተያና ማከሚያ ማዕከላት ለሚከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በዲላ ከተማ በንግድ ሥራ የተሰማራ አንድ ወጣት ለ41 አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።


ድጋፉን ያደረገው ወጣት ሀቢብ ሻፊ ከኮሮና ጋር ተያይዞ ለችግር ከሚጋለጡ ወጎኖች መካከል አካል ጉዳተኞችና አረጋዉያን ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግሯል።

ከ155 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ16 አካል ጉዳተኞችና የዓይነ ስውራን ዊልቸርና ብትር እንዲሁም ለቀሪዎቹ የስንዴ ዱቄት፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብል፣ የእጅ ጓንትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

ድጋፉ ከተደረገላቸው ዓይነ ስውራን መካከል ወይዘሮ ብርቱኳን ጎበና በሰጡት አስተያየት በእጃቸው ብትሩ ባለመኖሩ ምክንያት በቤት ውስጥ እንኳን ለመንቀሳቀስ ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በዲላ ከተማ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ13 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ አረጋዉያንና አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ መረጋገጡን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ ናቸው።

በእነዚህ ወገኖች ላይ ኮሮና የሚያድርሰውን ጫና ለመቀነስ የከተማ አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ መሆኑንና ወጣቱ ያደረገውም አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም