ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ ወገኖች የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ ወገኖች የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30/2012 (ኢዜአ) ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስገነዘቡ።
ሚኒስቴሩ 'አይሰለጥንብኝም' ከተሰኘ የጸረ-ሱስ ንቅናቄ በጎ አድራጎት ግብረ ኃይል ጋር በመሆን የደም ልገሳና ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም በሱስ ውስጥ የሚገኙት ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።
እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ በቀላሉ ሊጠቁ እንደሚችሉ ነው ያስገነዘቡት።
እንደሚኒስትሯ ገለጻ፤ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የበሽታ መከላከል አቅማቸውን ማጠናከርና ሌሎች ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል።
ከበሽታው ራስን ለመጠበቅ የሌሎችን እርዳታ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሱስ ውስጥ የሚገኙትም ለመጠበቅ ጥረት እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት።
ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምና በጎ ተግበራትን በማከናወን ከሱስ ለመላቀቅ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ይህም መልካም ስራን መስራት የሚለማመዱበትና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም እራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ ያግዛል ብለዋል።
የአይሰለጥንብኝም የጸረ-ሱስ ንቅናቄ በጎ አድራጎት ግብረ ሃይል ፕሬዚዳንት መጋቢ ቢኒያም አዱኛ በበኩላቸው ''የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለማለፍ የጋራ ጥረትና በጎ ተግባራትን ማጠናከር ያስፈልጋል'' ብለዋል።
በሱስ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም በበጎ ስራዎች ላይ በመሰማራት ከሱስ የሚወጡበት አጋጣሚ ሊያደርጉት እንደሚገባ መክረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ የበሽታ መከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ተገቢ ነው።
ደም የለገሱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች በበኩላቸው በደም እጦት ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን መታደግ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።
ከለጋሾቹ መካከል ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቶማስ ኩዊ በዚህ አስከፊ ጊዜ በደም እጦት ህይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችን ለመታደግ እንደ አንድ ዜጋ ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መሰለች ደጀኔ በበኩላቸው ደም መስጠት ከራስ ሳይጎድል ሰውን የማገዝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።