በታች አርማጭሆ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በታች አርማጭሆ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ
ጎንደር፣ ሚያዚያ 30/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ 37 ክላሽን ጠብመንጃና በርካታ ጥይቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወረዳው ሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ገለፀ ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አንተነህ ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት ጠመንጃውና ጥይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ በሳንጃ ኬላ ላይ በተካሄደ ጥብቅ ፍተሻ ነው።
ዛሬ ረፋድ ላይ የጸጥታ አካላት በኬላው ባካሄዱት ጥብቅ ፍተሻ ከተያዘው 37 ክላሽን ጠብመንጃ በተጨማሪ 9ሺህ 277 የክላሽ ጥይትና 21 የክላሽ ጥይት መያዣ ካዝናዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው ሲጓጓዝበት የነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 አአ 44648 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ከነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
አሽከርካሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ሲሆን ከሾፌሩ ጋር የነበረ ሌላ አንድ ግለሰብም በድርጊቱ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው መነሻው ምእራብ ጎንደር ዞን ምድረ ገነት ከተባለው ከተማ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር ባይውል ኖሮ የአካባቢውን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥል እንደነበርም አቶ አንተነህ ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችን ለህግ እንዲቀርቡ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡