በምዕራብ ወለጋ ኮሮናን ለመከላከል በዞኑ መግቢያና መውጫ በሮች ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ኮሮናን ለመከላከል በዞኑ መግቢያና መውጫ በሮች ቁጥጥር እየተደረገ ነው
ነቀምቴ፣ ሚያዝያ 30/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በዞኑ መግቢያና መውጫ በሮች ላይ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የክትትልና ቁጥጥር ስራው እየተካሄደ ያለው ዞኑን ከጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚያዋስኑት በተለይም በዳቡስ ኬላና ሌሎች መተላለፊያ በሮች ላይ ነው።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ ይማሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰዎች ሲወጡም ሆነ ሲገቡ በዳቡስ ወንዝ አቅራቢያ በሙቀት ልኬት እንዲያልፉ እየተደረገ ነው።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ጋር ተወያይተው ከዳቡስ ኬላ በተጨማሪ በሌሎች አዋሳኝ ወረዳዎች የፀጥታ አካላት የጥበቃ ስራን በማጠናከር የሚገመቱ ሰዎች ለጥንቃቄ በማቆያ እንዲሆኑ ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በዞኑና በክልሉ ካለው ግብረ ኃይል ጋር የተከናወኑ ተግባራት ላይ በየቀኑ በስልክ እየተገናኙ እየገመገሙ መሆናቸውንም አቶ ተካልኝ አስረድተዋል፡፡
የዞኑ የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳለ ወጋሪም በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ አካላት ጋር ጥምረት በመፍጠር በሁለቱም በክልል ያሉ የፀጥታ አካላት እየተናበቡ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከቤጊ፣ ቦጂ ድርመጂ፣ ነጆና ቂልጡ ከራ ወረዳዎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ከክልሉ አዋሳኝ ወረዳዎች አመራሮች ጋር በመወያየት ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተጠናከረ ቁጥጥር ለማድረግ ተስማምተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ፀሐፊ አቶ መሠረት መንገሻ ናቸው።
ከምዕራብ ወለጋ ወደ አሶሳ ከአሶሳ ወደ ምዕራብ ወለጋ የሚገቡና የሚወጡ መንገደኞች በዳቡስ ኬላ ላይ ለጥንቃቄ በሙቀት ልኬት እየታየ እንዲያልፉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዞኑ ስድስት ወረዳዎች የማቆያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አቶ መሠረት አመልክተዋል።