በድንበር አካባቢ ወረርሽኙን የመከላከል ሥራ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በድንበር አካባቢ ወረርሽኙን የመከላከል ሥራ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል
ሀዋሳ ሚያዝያ 30/2012 (ኢዜአ) በመግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን በክልሎች መካከል ያለው የቅንጅት ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት "በክልሉ የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ሥራ በድንበርና በክልሉ መግቢያና መውጫ በሮች አካባቢ በትኩረት እየተሰራ ነው።"
ክልሉ ከኬኒያና ደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው በሮች በኩል በፀጥታውም ሆነ በጤናው መዋቅር ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከደቡብ ሱዳን በሚዋሰነው የድንበር መግቢያ እስካሁን ያለው የሥጋት ደረጃ መጠነኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን በሞያሌ መስመር አቅጣጫ ባሉ የክልሉ መግቢያና መውጫ በሮች በኩል የሚከናወነው የመከላከል ሥራ እጅግ ፈታኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደረገው በሞያሌ ከሚዋሰኑ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል ያለው የቅንጅት ክፍተት እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአብነትም በቅርቡ ከኬኒያ በሞያሌ በኩል ገብቶ በዳዋ ማቆያ ምርመራ ያደረገና ቫይረሱ የተገኘበት አንድ ግለሰብ የምርመራ ውጤቱ ከመገለጹ በፊት ከሌሎች 41 ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ደቡብ ክልል መግባቱን አስታውሰው፤ ግለሰቡንና አብረውት የተጓዙ ሰዎችን ለመያዝ የተደረገው ጥረት ፈታኝ እንደነበረ ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ችግሮችን እንዳይገጥሙ ብሎም ስኬታማ የመከላከል ሥራ መስራት እንዲቻል ክልሎች ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር ሊዘረጉ እንደሚገባና በዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥትም በትኩረት መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል።
በክልሉ የምርመራ አቅምን ለማሳደግ በተለይ የቤት ለቤት አሰሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተደራሽ መደረጋቸውን አስረድተዋል።
ከሀዋሳ በተጨማሪ በሌሎች ከተሞች ላይም የምርመራ ማዕከላትን የመክፈት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው አሁን ላይ የወላይታ ሶዶ ማዕከል ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ክልሉ ከደቡብ ሱዳንና ኬኒያ ጋር በሚዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች አምስት መውጫና መግቢያ በሮች ተለይተው ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በእነዚሁ በሮች ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል በቅንጅት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ተግባር በተገቢው መንገድ እየተከናወነ እንዳለ ገልጸዋል።