የአስም ሕሙማን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ ይገባል...ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአስም ሕሙማን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ ይገባል...ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2012(ኢዜአ) የአስም ሕሙማን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ የሚከበረውን የአስም ቀን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የአስም በሽታ የአየር ቱቦ መጥበብ የሚያመጣ በሽታ ሲሆን፣ በአካባቢያዊ ተጽዕኖና ዘረመል በሆኑ ጉዳዮች የሚመጣ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው።
በዓለም ደረጃ 358 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል፤ በየዓመቱ 460ሺህ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይወታቸው እንደሚያልፍ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 3 ነጥብ 6 በመቶ በሽታው ያለበት ሲሆን፣ በዓመት ከሚመዘገበው 100 ሺህ ሞት ስምንቱ የሚሞቱት በዚህ በሽታ ነው።
በሽታው የመተንፈሻ አካላትን ጥቃት ስለሚያደርስ ሕሙማኑ ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን እንደተናገሩት፤ የአስም ሕሙማን ጥንቃቄያቸውን ሊያዳብሩ ይገባል።

የኮሮና ቫይረስ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ላይ እንደሚበረታና ከነዚህም አስም አንዱ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጓዳኝም የእጅ ንጽሕናንና አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንዲሁም በቤት ውስጥ በመቀመጥ ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሄል አርጋው በበኩላቸው የአስም ሕሙማን በሽታውን ከሚያባብሱ ሁኔታዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በተለይም የኮሮና ቫይረስ በሚያሳድርባቸው ጫና የሕመም ስሜት መባባስ ካጋጠማቸው ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ጎን ለጎንም በየዕለቱ የሚወሰዱትን የአስም መድኃኒት በሕክምና ባለሙያዎች እንደታዘዙ በአግባቡ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
ለድንገተኛ የአስም ሕመም የሚወሰደው መድኃኒት በተለይም በአፍ የሚነፉትን በቤታቸው በበቂ መጠን እንዲያስቀምጡም አስገንዝቧል።
የበሽታውን ቀስቃሽ ነገሮችን፣ ጭንቀትና ውጥረት ማስወገድ እንዲሁም ቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ያስፈልጋል ተብሏል።