ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በጋራና በሰላማዊ መንገድ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ገለጹ። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መካከል የሚስተዋለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ሁለቱ አካላት ጉዳያቸውን በሰላማዊና የእስልምና አስተምህሮት በሚያስቀምጠው መሰረት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። “መንግስት ማንንም አይደግፍም ማንንም አይቃወምም። ነገር ግን ሁለቱ አካላት ጠንካራና አንድ ሆነው በጋራ ቢሰሩ ለአገርና ለተቸገረ ወገን መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በሁለቱ አካላት መካከል ሰላም ለማውረድ የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ ለሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተጣለበትን አደራ እንደሚወጣ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል። የኮሚቴዎቹ አባላት በበኩላቸው ሙስሊሙ ማሕበረሰብ የሚያቀርበውን ጥያቄ ለመፍታት "ስሜቶቻችንን ገታ አድርገን በትብብር በመስራት ለውጥ እናመጣለን" ነው ያሉት። የኮሚቴው ሰብሳቢ ሐጂ ኡመር ኢድሪስና የእስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼሕ መሃመድ አሚን ጀማል እንደገለጹት ዛሬ የተቋቋመው ኮሚቴ የነበሩ ችግሮችን አርሞ ወደፊት ሕዝበ ሙስሊሙ አንድ ሆኖ በጋራ፤ ልዩነቶችም ሲኖሩ በጋራ በመመካከር እየፈታ ወደፊት የሚሔድበትን አቅጣጫ የሚቀይስ እና ሕዝብ ሙስሊሙ እስካሁን የሚፈልጋቸው መንፈሳዊና የልማት ስራዎችን ጭምር ተጠናክሮ የሚሔድበት የጋራ ተቋም ነው፡፡ ከኮሚቴው ብዙ ሃላፊነቶች እንደሚጠበቁበት ገልጸው፤ ኃላፊነተቸውን ይወጣሉ የሚል ትልቅ እምነትና ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አቡበከር አሕመድና አሕመዲን ጀበል በበኩላቸው "በዛሬው ቀን ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ሲናፍቀው የነበረውን ለማሳካት ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንደሚሉት ተደምሮ እኩል እንደ ዜግነት ተሳታፊ የሚሆኑት ስራ ለመስራት ጠንካራ ተቋምና መሪ የሚፈጠርበትን ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ሙስሊሙ ማሕበረሰብ እንደ ዜጋ የእድገት፤ ብልጽግና፤ ሰላምና ልማት ተሳታፊ የሚሆኑበትን ስራ ለመስራት ኃላፊነት ተቀብናል” ብለዋል፡፡ ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም የሙስሊሙ ማሕበረሰብ ከሔደባቸው መስመርና ከለፋባቸው ልፋት አንፃር የአቅማችንን ሁሉ አድርገን የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ለለውጡ እንቅስቃሴ ጠንካራ ደጋፊ በመሆን የተጀመረው ጉዳይ ከግብ እንዲደርስ ሁሉም ከጎን እንዲቆም አደራ እንላለን" ብለዋል ኮሚቴዎቹ፡፡ ኮሚቴው ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፤ የሙስሊሙ ማሕበረሰብ ከማንኛውም ልዩነቶች አውጥቶ በትብብር መስራትና ሁሉም የሚቀበለው የተጠናከረ የእስልምና ጉዳዩች የሚመሰረትበትን አቅጣጫና ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል ነው ያሉት።