ቀጥታ፡

በጋምቤላ ለኮሮና መከላከል ከ14 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ጋምቤላ፣ ሚያዚያ 30/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከ14 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ መገኘቱን የክልሉ ሀብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የግብረ ኃይሉ  ሰብሳቢና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ  የተገኘው ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ነው።

ከተገኘው ድጋፍ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና ቀሪው በዓይነት የተለገሰ መሆኑን አመልክተዋል።

የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢ የዞኖችና የወረዳዎች ሪፖርት ተጠቃሎ ሲደርስ ድጋፍ  ከጠቀሰው አሃዝ በላይ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

"በቀጣይም የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር በማጠናከር የኮሮና ቫይረስ ሊያደረስ የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከል ይሰራል" ብለዋል

የኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ህብረተሰቡ የጀመረውን የመደጋገፍ ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ የማነ ተስፋዬ በበኩላቸው  የከተማው ነጋዴዎችና ሌላም ነዋሪ ለአቅመ ደካማ ወገኖች  የተለያዩ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ  እያደረጉ ነው ብለዋል።

እስካሁንም ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አህመድ ኢላዲ በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስን ችግር ለማለፍ እርስ በእርስ የመደጋገፍ  ባህላቸውን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ለአቅመ ደካማ ወገኖች  ያላቸውን በማካፈል የጀመሩትን ድጋፍ  እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለሚቸገሩ አቅመ ደካሞች የጀመሩትን የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ ደረጀ ፈይሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም