ቀጥታ፡

በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ላይ የሚታየውን መዘናጋት ለማስወገድ እየተሰራ ነው

ፍቼ፣ ሚያዝያ 30/2ዐ12 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ላይ የሚታየውን መዘናጋት ለማስወገድ ተገቢው የጥንቃቄና የሕግ ማስከበር ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ። 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የዞኑ ነዋሪዎች ግን የኅብረተሰቡ መዘናጋት አሁንም ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት አመላካች ነው ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ምክትል ሰብሳቢ አቶ አጥናፉ በቀለ ዛሬ እንደገለጹት በዞኑ አሥራ ሦስት ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በሽታው የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኅብረተሰቡ ግንዛቤውን አዳብሮ የጥንቃቄ ሥራዎችን ሳይዘናጋ እንዲያከናውን ከጤና ባለሙያዎች፣ ከፖሊስ፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከአካባቢ ሚሊሽያ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የእምነት፣ የገበያና የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ እጁን በአግባቡ እንዲታጠብና አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ ከማስተማር ጐን በሽታውን ለመከላከል በቅርቡ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም ኅብረተሰቡን ለበሽታው አጋላጭ በሆነ ሁኔታ ወጣቶችን ሰብስበው የተገኙና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 51 የጫትና የሺሻ ቤቶች እንዲዘጉና ሕግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ ማድረጉን ተናግረዋል። 

በኅብረተሰቡ ላይም አላስፈላጊ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ በመጨመር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 45 የንግድ መደብሮች በገንዘብ ተቀጥተዋል።

ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ሊታረሙ ያልቻሉ ዘጠኝ የእህል መጋዘኖችም እንዲዘጉ ተደርጓል።

ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠርም ግብረኃይሉ ባደረገው ጥረት 640 ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይትና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብና ለስላሳ መጠጦች እንዲወገዱ ማድረጉን አቶ አጥናፉ ገልጸዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የዞኑ ነዋሪዎች የኅብረተሰቡ መዘናጋት በሰፊው እንደሚታይ ገልጸው ሕዝቡ ራሱንና ሌላውን ለማዳን የግብረኃይሉን ሥራዎች ማገዝ አለበት ብለዋል ።

ከፍቼ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ አቶ ማሞ በላቸው እንደገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈጸም ረገድ በፀጥታ ኃይሉ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በቂ ባለመሆናቸው በገበያና በእምነት ሥፍራዎች ጥንቃቄ የጎደለውና ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም