ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በነሐሴ ወር የማጣሪያ ጨዋታ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በነሐሴ ወር የማጣሪያ ጨዋታ አለበት
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በታንዛንያ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታ ታደርጋለች። በውድድሩ ላይ የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በታንዛንያ የሚካሄድ ይሆናል። የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እንድታስናግድ ካፍ የመረጣት ታንዛንያ የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ክፍለ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎችንም ታስተናግዳለች። በዚሁ መሰረት የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ሴካፋ ጨዋታዎች በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄዱ ይሆናል። በምድብ አንድ ሩዋንዳ፣ቡሩንዲ፣ ሶማሊያና ሱዳን ሲሆኑ፤ በምድብ ሁለት ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኡጋንዳ ጋር ተደልድላለች። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ በታንዛንያ በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፉ አገራትን ለመለየት በሰባት መደብ ከፋፍሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋል። በሰባቱ ውድድሮች አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር መሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ። በታንዛንያው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከአንድ እስከ አራት የሚወጡ ብሔራዊ ቡድኖች ከመስከረም 7 እስከ 28 ቀን 2012 ዓ.ም በፔሩ በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው ይሳተፋሉ። በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም በቡሩንዲ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ተሳትፎ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሶማሊያ ጋር በነበረው ጨዋታ ሶስት ተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ክስ ቀርቦባቸው ከውድድሩ እንዲሰናበቱና አንድ ጨዋታ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል። ተመስገን ዳና የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት ላይ ይገኛል።