ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ጥቂት የህወሃት አመራሮች በሚፈጥሩት ፕሮፓጋንዳ መደናገጥ የለበትም... ትዴፓ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2012(ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ጥቂት የህወሃት አመራሮች በሚፈጥሩት ፕሮፓጋንዳ መደናገጥ የለበትም ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።

አመራሮቹ ምርጫ እናካሂዳለን የሚሉት ለህዝቡና ለህገ-መንግስቱ ተጨንቀው ሳይሆን የራሳቸውን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ነው ብሏል። 

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጊደና መድሕን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት ምርጫውን ለማራዘም መወሰኑ ለህዝቦችና ለአገር ደህንነት ከመጨነቅ ባለፈ ህገ-መንግስቱን ማክበሩን ያሳያል ብለዋል።

''አለምአቀፉ ወረርሽኝ የኢትዮጵያ ስጋት ከሆነ የትግራይ ህዝብ ስጋት የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም'' ያሉት አቶ ጊደና፤ ክልሉን እያስተዳደረ ያለው መንግስት ግን ከህዝብ ደህንነት ይልቅ ስልጣኑ የሚያሳስበው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወረርሽኙ በሰዎች ህይወት ላይ የደቀነውን ስጋት ወደ ጎን ጥሎ ምርጫ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመር ለዚህ ማሳያ መሆኑንም ተናግረው፤ የትግራይ ህዝብ ጥቂት የህወሃት አመራሮች በሚፈጥሩት ፕሮፓጋንዳ መደናገጥ የለበትም ብለዋል።

ሰሞኑን የትግራይ ክልል ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እንደሚያደርግ ማስታወቁም ጥቂት የህወሃት አመራሮች የራሳቸውን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ካላቸው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን አንስተዋል።

ወረርሽኙ በህዝቦች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ እየታወቀ ወረርሽኙን ለመከላከል ርብርብ ከማድረግ ይልቅ ለስልጣን መሽቀዳደም በህዝብ ዘንድም ተዓማኒነትን የሚያሳጣ ነው ብለዋል።

''ህወሃት ለህገ-መንግስት ተቆርቋሪ ነኝ ካለ በህገ-መንግስቱ የተቋቋመውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማክበር ነበረበት'' ያሉት ሃላፊው "ህግ እየጣሱ ህግ ለማስከበር መሞከር ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

የትግራይ የኢትዮጵያ አካል እንደመሆኑ የፌዴራል መንግስት  ምርጫው እንዲራዘም የወሰነውን ውሳኔ ህዝብና አገርን ያስቀደመ በመሆኑ የክልሉ ህዝብም ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።

መንግስት ምርጫውን አስመልክቶ የተሻሉ አማራጮችን እየፈለገ ባለበት ወቅት ሕዝብንም ሆነ አገርን የማይጠቅም ምርጫ ለማድረግ መነሳት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ መንግስት የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ህገ መንግስቱን የሚጥሱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም