የግል ድርጅቶች በኮቪድ-19 የተከሰተውን ቀውስ በማምረትና ሠራተኞቻቸውን ሳያሰናብቱ ማለፍ አለባቸው-ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
የግል ድርጅቶች በኮቪድ-19 የተከሰተውን ቀውስ በማምረትና ሠራተኞቻቸውን ሳያሰናብቱ ማለፍ አለባቸው-ተቋማት
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ) በኮቪድ-19 የተከሰተውን ቀውስ የግል ድርጅቶች እያመረቱ ሠራተኞቻቸውም ሥራቸውን ሳይለቁ በጋራ ማለፍ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ ገለጸ።
ድርጅቶቹ ሠራተኞቻቸውን በሥራ ላይ ከማቆየት ባለፈ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።
ቢሮው ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽንና የኢትዮጵያ ራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ጋር በመሆን የሆራይዘን አዲስ ጎማና የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማኅበር የኮቪድ-19 መከላከል ላይ ያተኮረ ምልከታ አድርጓል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተክሌ ደሬሳ እንዳሉት፤ ወረርሽኑን ለመከላከል ሁለቱ ኩባንያዎች የሚያደርጉት ቅድመ ጥንቃቄ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው።
በድርጅቶቹ በስራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፤ የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር)ና አልኮል፤ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ መታጠቢያ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
''ኪሳራ ገጥሞናል'' ወይም ''የገንዘብ እጥረት ገጥሞናል'' በሚል ሰበብ ሠራተኞችን ለማሰናበት የሚፈልጉ ድርጅቶች ከኩባንያዎቹ ትምህርት ወስደው ችግሩን ተደጋግፈው ማሳለፍ አለባቸው ብለዋል።
በመዲናዋ ከ300 በላይ ድርጅቶች ''የገንዘብ እጥረት ገጥሞናል'' የሚል ቅሬታ እንደሚያቀርቡና በርካታ ሠራተኞችም ያለአግባብ ከሥራ ተቀንሰናል የሚል ቅሬታ እንደሚያቀርቡ አቶ ተክሌ ገልጸዋል።
በመሆኑም"የመጣውን አስከፊ ወቅት ድርጅቶች ማምረት ሳያቆሙና ሠራተኞችን ከሥራቸው ሳይፈናቀሉ" በጋራ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል የመንግሥት ሥራ ብቻ አይደለም በሚል ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ድርጅቶችም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ" ድርጅቶቹ ለሠራተኞች ለሚያደርጉት እንክብካቤ" ምስጋና አቅርበዋል።
"የገጠመንን አስከፊ ችግር በጋራ የምናልፈው በመሆኑ" ዛሬም እንደትናንቱ በጋራና በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበር የሰው ኃይል ዳይሬክተር አቶ ብሩክ አዱኛና የሆራይዘን አዲስ ጎማ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አበበ ለደህንነት ቅድሚያ መስጠት የድርጅቶቹ ተቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
ማንኛውም ወደ ድርጅቶቹ የሚገባ ሰው ሙቀቱን ይለካል፤ የአፍ መሸፈኛና የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር) ወይም አልኮል ይቀርብለታል፤ ከእጅ ንክኪ የሆነ መታጠቢያም ተዘጋጅቶለታል ብለዋል።
መንግሥት ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያወጣቸውን መመሪያዎች መሠረት በማድረግ የቅድመ መከላከል ስራዎችን እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ በማስጨበጥና የመከላከያ ግብዓቶችን በማቅረብ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በሥነ ምግባር ችግር ካልሆነ አንድም ሠራተኛም እንደማይቀነስ ኃላፊዎቹ አረጋግጠዋል።