ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በ20ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳለፈ

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 20ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በቀረቡለት አራት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል።

ምከር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናትና የአብያተ ክርስቲያናት ህብረቶች ያቋቋሙትን ሀገር አቀፍ ተቋም የህግ ሰውነት መስጠት ተገቢ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ ላይ ነበር፡፡

የትራንስፖርት ዘርፉ ዝርዝር የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ መስተጋብሮቻችን በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ የተቀናጀና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ሊመራበት የሚገባውን አቅጣጫ ማስቀመጥ የፖሊሲው ዋነኛ ትኩረት ነው፡፡

የፖሊሲ ሰነዱ የትራንስፖርት ዘርፉ ተቋማዊና አስተዳደራዊ አደረጃጀቶች ሊከተሉት የሚገባውን ስትራቴጂ በመለየት ሊያሳኩት የሚፈለገውን ግብ፤ የገጠርና የከተማ ትስስር፤ የከተማ ለከተማ ትስስር፤ ዓለም ዓቀፍ ትስስር፤ እንዲሁም ከአካባቢያው ሃገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠንከር የአገሪቱን እድገት በማስቀጠል ረገድ ሚናውን እንዲጫወት ለማድረግ ሰነዱ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው ጉዳይ በሎጀስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲ ላይ ነበር፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማጎልበት በየዘርፉ የተለያዩ የፖሊሲ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ያወሳው መግለጫው፣ ይሁንና ፖሊሲ የተቀረጸላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ሲተገበሩ ለዘርፎቹ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ዘርፍ በፖሊሲ መደገፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል።

የዘርፉን አመራር፤ አደረጃጀትና አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ፤ በሎጅስቲክስ መሰረተ ልማት ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ፤ እንዲሁም የሎጅስቲክስ ዘርፍ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ከሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ጋር ተደጋጋፊ ሆኖ አንዲያድግ ለማስቻል ብሔራዊ የሎጂስቲክ ዘርፍ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

በመጨረሻ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ በመሆኑና የአገሪቱን የልማት እቅድ የሚያስፈጽም አቅም እንዲኖረው የባንኩን ካፒታል ማሳደግ በማስፈለጉ የባንኩን ካፒታል ማሳደጊያ የማሻሻል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም ረቂቅ ደንቡን በማጽደቅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም