ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የኮሮናን በመከላከልና መቆጣጠር ስራው የላላ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የኮሮናን በመከላከልና መቆጣጠር ስራው የላላ ነው ተባለ
መተማ ኢዜአ ሚያዚያ 29/2012 በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ጋር በሚዋሰኑ ቦታዎች የኮሮና ቫይረስ ቁጥጥር የላላና የለይቶ ማቆያ ማእከላቱ ደግሞ የግብዓት እጥረት እንዳለባቸው የፌደራል የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
ከፌደራልና ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል የተወጣጣ ልዑክ ቡድን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
በግብረ-ኃይሉ የድንበር ቁጥጥር ሰብሳቢና የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን እንዳሉት ኢትዮጰያና ሱዳን የሚያዋስናቸውን ሰፊ ድንበር በመኖሩ ለኮሮና መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
በተለይም በሱዳን ያለው የወረርሽኙ ስርጭት መስፋትና በድንበር አካባቢ የሚታየው የላላ ቁጥጥር ለዞኑና ክልሉ ህዝብ ብሎም ለሀገሪቱ ስጋት የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል።
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በርካታ ዜጎች በመኖራቸው በድንበር አካባቢ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከማድረግ ባሻገር በሙቀት ልኬት ብቻ የሚገቡ ዜጎች በመኖራቸው ቫይረሱ ይዛመታል የሚል ስጋት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሰለሆነም በድንበር አካባቢ ያሉ የዞኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ህዝብ ከፀጥታ አካሉ ተሰውረው የሚገቡ ዜጎችን በመለየት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት የራሳቸውና የመላ ሀገሪቱ ህዝቦችን ጤና ከወረርሽኙ መታደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዞኑ በተለዩ የማቆያ ማእከላት ያለው የግብዓት እጥረትም ውጤታማ የመከላከል ስራ እንዳይሰራ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
"ከፍተኛ የሆነ የምግብና የውኃ አቅርቦት ችግር እንዲሁም የህክምናና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን ተመልክተናል" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው የሚመለከተው አካል ለዞኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ችግሩን መፍታት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች ሙሉ ከመተማ ዮሃንስ ኢምግሬሽን ጉዳዮች ቅርንጫፍ መረጃ ጋር ወጥ ሆኖ መያዝ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
በኮኪት ከተማ በተዘጋጀው የማቆያ ቦታ 37 ዜጎች ሾልከው መጥፋታቸውን ጠቅሰው በለይቶ ማቆያ ቦታ ለቁጥጥር የሚመደቡ የፀጥታ አካላት ኃላፊነት ወስደው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው ከሱዳን በሚያዋስኑ አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ ጥበቃና ክትትል ይደረጋል።
በዞኑ በተለዩ የማቆያ ቦታዎች የሚመደቡ የፀጥታ አካላት ቁጥርን በማሳደግ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በማቆያ ቦታዎች መደበኛ የሆነ የፀጥታ አካል በዞኑ ሰላምና ደህንነት ቢሮ በኩል እንዲመደብም አስታውቀዋል፡፡
በድንበር ጫካን ከለላ አድርገው የሚገቡ ግለሰቦችን ለመያዝና ለመቆጣጠርም በየቀበሌው ለሚገኝ ሚሊሻ ስምሪት በመስጠት ለመከላከል ብርቱ ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
በአካባቢው ኮሮናን ለመከላከል የሚረዱ ግብዓቶችን ለሟሟላት የጤና ሚኒስቴር፣ የምግብ ዋስትና አደጋና መከላከል እንዲሁም የፀጥታ አካላት ተባብረው እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢና ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ በበኩላቸው የበጀትም ሆነ የግብዓት አቅርቦት እጥረት ቢኖርም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አቅም በፈቀደ መጠን እየተሰራ ነው ብለዋል ።
በተለይም ከሱዳን ወደ ኢትዮጰያ የገቡ 3 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በሙቀት ልኬት እንዲያልፉ መደሩን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም 600 የሚሆኑ ዜጎችን ለ14ቀናት በለይቶ ማቆያ ገብተው ጤንነታቸው በመረጋገጡ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ገልፀዋል፡፡
ነገር ግን በድንበር በጫካ የሚገቡት ዜጎች መኖራቸውን ገልፀው እስካሁን በተሰራ የቁጥጥር ስራም 86 ዜጎች ተይዘው በማቆያ ቦታ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
ዞኑ ለቫይረሱ ስርጭት የተጋለጠ በመሆኑ የፌደራልና የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል፡፡