በኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ የፀሃይ ግርዶሽ ይከሰታል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ የፀሃይ ግርዶሽ ይከሰታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ እንደሚከሰት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ግርዶሹ ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚታይ ሲሆን ክስተቱም ወለጋ፣ ከፊል ጎጃምና ጎንደር፣ በወሎ በተለይ ላሊበላ አካባቢ ቀኑ የሚጨልም ይሆናል ተብሏል።
በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ደግሞ በዕለቱ በከፊል ጨለማ ሊሆን እንደሚችል የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን በላይ ተናግረዋል።
ግርዶሹ ስድስት ሰዓታት የሚፈጅ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር የፊታችን ሰኔ 14 እሁድ ቀን ከጠዋቱ 12፡45 እስከ ቀኑ 6፡33 የሚቆይ ይሆናል።
ዋናው ቀለበታዊ ግርዶሽ የሚከሰትበትና ቀኑ የሚጨልምበት ሰዓት በዕለቱ ከጠዋቱ 3፡45 ላይ ሲሆን ለ38 ሰከንድ የሚቆይ ይሆናል ነው ያሉት።
የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሐይና መሬት መሃከል ስትገባና ፀሐይን እንዳናያት ስትጋርድብን የሚከሰት መሆኑን ዶክተር ሰሎሞን አስረድተዋል።
ይህ ክስተት ኢትዮጵያውያን በዘመናቸው ሊያዩት የሚችሉት አስደማሚ የተፈጥሮ ክስተተ ሲሆን በቀጣይ ይህ ቀለበታዊ ግርዶሽ የሚታየው ከ18 ዓመት በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
''በግርዶሹ ሳቢያም በሚፈጠረው ጨለማ ህብረተሰቡ እንዳይደናገጥ አስቀድሞ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል'' ብለዋል።
በእለቱም የሙቀት መጠን የንፋስና የደመና እንቅስቃሴ ስለሚቀየር የአየር ሁኔታ ይዛባል፤ በተወሰነ መልኩ የኤሌክትሪክ ፍጆታም ይጨምራል ብለዋል።
ግርዶሹ በሚፈጠርበት ሰዓት የጨረቃ ትክክለኛ ቅርጽና የመሬትና የፀሐይ ልኬት የሚደረገው ጥናት በዚሁ ወቅት በመሆኑ ተማሪዎች፣ ተማራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም ጠቁመዋል።
ክስተቱ ዓለም ዓቀፍ ሲሆን ከማዕከላዊ አፍሪካ ኮንጎ ተነስቶ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኦማን፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ታይዋን፣ ህንድ እና ቻይናን አቋርጦ ፓስፊክ ውቂያኖስ ላይ እንደሚያበቃም ተገልጿል።
''ኢትዮጵያ ለግርዶሹ ተስማሚ የደመና፣ የሙቀት መጠንና ግርዶሹ በግልጽ የሚታይባት መሆኑን የተደረገው ጥናት አመልክቷል'' ብለዋል።
በተጨማሪ ለጎብኚዎች አመቺና ጥንታዊ አገር መሆኗ የውጭ ጎብኚዎችና ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ላሊበላ ከተማ የግርዶሹን ሁነት እንዲከታተሉ ተወስኗል።
ነገር ግን በወቅታዊ የኮሮናቫይረስ መከሰት ጎብኚዎቸ ከአገር አገር ስለማይንቀሳቀሱ ሁነቱን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ እንዲከታተሉ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜና ረጅም ዘመናት የጸሃይ ግርዶሽ መከሰቱ መረጃዎች ያሳያሉ።