ለችግር ለተጋለጡ 7 ሺህ 600 ሰዎች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለችግር ለተጋለጡ 7 ሺህ 600 ሰዎች ድጋፍ ተደረገ
አክሱም፤ ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ/) በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በኮሮና ቫይረስ ስጋት ዕለታዊ የምግብ ፍጆታ ማግኘት ላልቻሉ 7 ሺህ 600 በላይ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እንደተደረገላቸው የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለፀ ።
በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል የኦፕሬሽን ፣ ሎጂስቲክስና አስቸኳይ ግብረ መልስ አስተባባሪ አቶ ልኡል ሃይለስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል ጎን ለጎን ለተቸገሩ ወገኖችም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በዞኑ ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ማህበራት ፣ባለሃብቶችና ከማህበረሰቡ በአንድ ወር ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ ኩንታል የምግብ እህል በድጋፍ ተለግሷል።
ከምግብ እህል በተጨማሪ 8 ሺህ 500 ሊትር የምግብ ዘይት እና የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶች ከተለያዩ ወገኖች በድጋፍ መሰባሰቡን ገልጸዋል።
ድጋፉ የቫይረሱ ስርጭት በፈጠረው ጫና ምክንያት ሰርተው እለታዊ የምግብ ፍጆታቸው ለመሸፈን ላልቻሉና ለአቅመ ደካሞች እንዲከፋፈል ተደርጓል።
በድጋፉ 7 ሺህ 600 ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው መድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳና በድጋፍ መልክ የተገኘው 255 ሺህ ሊትር የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ለተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች መከፋፈሉንም አቶ ልኡል ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ባደረገው የድጋፍ ጥሪ መሰረት ዞኑ 5 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
አንድ ኩንታል የምግብ እህልና 50 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት ድጋፍ እንደተደረገላቸው የገለጹት የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ጸሃይነሽ ሀይሉ፤ በችግር ጊዜ ለደረሱላቸው ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል።
በአሕፈሮም ወረዳ የእንትጮ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትርሓስ ሓጎስ በበኩላቸው 50 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄትና አምስት ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ እንደተደረገላቸውና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አንድ ኩንታል እህልና 500 ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እንደተሰጣቸው የተናገሩት ደግሞ በመረብ ለኸ ወረዳ የራማ ከተማ ነዋሪ አቅመ ደካማ አቶ ስዩም መኮነን ናቸው ።