ቀጥታ፡

ድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከያ ጸረ-ተህዋሲያን መርጫዎችን ድጋፍ አደረገ

 አዲስ አበባ  ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ)  ''ክሮፕሴቭ ትሬዲንግ'' የተሰኘ የግል ድርጅት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ጸረ-ተህዋሲያን መርጫዎችን ዛሬ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመገኘት የተቋቋመው ለብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው አስረክቧል።

የጸረ-ተህዋሲያን መርጫዎቹ 150 የሆኑ ባለ20 ሊትር ተሸካሚና 10 ባለ 10 ሊትር ተሸካሚ እንደሆኑ ተገልጿል።

መሳሪያዎቹ ለህክምና መስጫ አካባቢዎች፣ ቫይረሱ ይገኝባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ ለይቶ ማቆያዎች የሚያገለግሉ መሆኑንም ተጠቁሟል።

ድጋፉን የብሄራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተረክበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ድርጅቱ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

''በዚህ ፈታኝ ወቅት እንዲህ ያሉና አረአያነት ያላቸው ተግባራት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ያስፈልገናል'' ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ተከስቷል ከተባለበት ወቅት አንስቶ ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብታቸውን በማካፈል አብሮነታቸውን ያሳዩበት መንገድ የሚደነቅ እንደሆነም ወይዘሮ አዳነች አንስተዋል።

ይህ ተግባር ዛሬም ያለመዘናጋትና ያለመሰልቸት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ዛሬ የተደረገው የኬሚካል መርጫ መሳሪያ የኮቪድ-19ን ምላሽ የሚያግዝ እንደሆነ አንስተዋል።

በዚህም መሳሪያዎቹ በህክምና መስጫ አካባቢዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙበት አካባቢ እንዲሁም በክልል ለሚገኙ የህክምና ተቋማት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።

የክሮሴቭ ትሬዲንግ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም እንግዳ በበኩላቸው ዛሬ ያደረጉት ድጋፍ ለህክምና መስጫ አካባቢዎች ሊያግዝ የሚችል በመሆኑ ድጋፉን እንደሰጡ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የኮሮናቫይረስን ለማስቆም ለሚደረገው ርብርብ የ300 ሺህ ብር ድጋፍ ለተቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።

''በአሁኑ ወቅት በዜጎች ዘንድ መዘናጋቶች እየተስተዋሉ ነው'' ያሉት አቶ አንዷለም፤ ወረርሽኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣ እንደመሆኑ የድጋፍ እጆች መዘርጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም የሚሰጡ የጤና ሚኒስቴር ምክሮችን እንዲተገብርና ራሱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም