ቀጥታ፡

ድንበር አቋርጠው የገቡ 83 ሰዎች በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸው ተገለፀ

አሶሳ፤ ሚያዚያ29 /2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር አቋርጠው ከገቡ 263 ሰዎች መካከል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው 83 ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባልና በጤና ቢሮው የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ በአቶ ዋጮ ዋቡልቾ ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ 263 ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ክልሉ ገብተዋል።

ከግለሰቦቹ መካከል150 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ቀሪ 113 ደግሞ ሱዳናዊያን ናቸው።

ግለሰቦቹ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ለይቶ ማቆያ እንደሚገኙ ጠቅሰው በየደረጃው ናሙናቸው ወደ ኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተላከ መሆኑን አቶ ዋጮ አስረድተዋል።

ወደ ለይቶ ማቆያው ከገቡት መካከል ባለፉት 14 ቀናት በተደረገ ምርመራ የ83 ሰዎች ውጤት ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ለይቶ ማቆያ ከሚገኙ ቀሪዎቹ 181 ሰዎች መካከል በዛሬው ዕለት ደግሞ የሌሎች 63 ሰዎች ናሙና ወደ ኢንስቲትዩቱ መላኩን ገልፀዋል።

የሃይማኖት አባቶችና በጎ ፈቃደኞች በለይቶ ማቆያ ማእከሉ  በመገኘት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የስነ-ልቦና ምክርና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አቶ ዋጮ ጠቁመዋል።

ለይቶ ማቆያ መግባት የቫይረሱ ተጠቂ መሆን አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ ከመረበሽ ይልቅ እውነታውን ከታማኝ ምንጮች በመረዳት ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም