ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና ግዥ ስርዓት ገንብታለች - የዓለም ባንክ

87
አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ሊሰጠው የሚችል የፋይናንስና ግዥ ስርዓት መገንባቷን የዓለም ባንክ አስታወቀ። የኢትዮጵያ መሰረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የፋይናስና ግዥ ስርዓት የሚገመግም ስብስባ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ተጀምሯል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ የገጠር የመንገድ ግንባታ፣ የውሃ ልማትና ንጽህና ላይ የሚሰሩ ሲሆኑ ከመንግስትና ከልማት አጋሮች በሚደረግላቸው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ የፋይናስና ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ያደርጋሉ። ባገኙት ድጋፍ አማካኝነት ተቋማቱ የሰሯቸው የፋይናስና ግዥ ስርዓት ውጤታማ መሆኑን መገምገም የስብሰባው ዓላማ ነው። የዓለም ባንክ ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ሚስ ናታሊያ ማይሌንኮ እንደገለጹት "ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት አስገራሚ የኢኮኖሚ ዕድገት አምጥታለች።" የኢኮኖሚ ዕድገቱ በጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ የገጠር የመንገድ ግንባታ፣ በውሃ ልማትና ንጽህና የሚሰሩ ተቋማት በሚሰጧቸው ያልተማከለ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ላይ በሰሯቸው ውጤታማ ስራዎች የታጀበ መሆኑን ገልጸዋል። በተቋማቱ ያልተማከለ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦት ውጤታማ ለመሆኑ ዋንኛው ምክንያት መንግስት በፌዴራል፣ በክልልና በወረዳ ደረጃ  የፋይናስና ግዥ ስርዓት የማስፈጸም አቅም በማጎልበቱ ነው ብለዋል። መንግስት የፋይናስና ግዥ ስርዓቱን ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ ይገባልም ነው ያሉት። ጠንካራ የፋይናስና ግዥ ስርዓት መገንባት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትና የልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንና በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው መንገድ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ለሰራችው ስራ ምስጋና እንደሚያቀርብ ነው ሚስ ናታሊያ የተናገሩት። ስርዓቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ፣ በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ የስራ ፍልሰት መቀነስና በዘርፉ ያሉ ስትራቴጂዎችን በጥልቀት ገምግሞ ተፈጻሚ ማድረግ በዋንኛነት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውንም አመልክተዋል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ሪፎርም ማስተባበበሪያ የቡድን መሪ አቶ ዳዊት ሽመልስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የፋይናንስና ግዥ ስርዓት እንዲኖራት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነች ነው ይላሉ። ሚኒስቴሩ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ የመንግስት የፋይናንስ ስትራቴጂ ዕቅድ ቀርጾ ወደስራ መግባቱን ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል መንግስት ተቋማት የፋይናንስና ግዥ መረጃዎችን ከሚኒስቴሩ ጋር የሚያስተሳሰር የኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንና በቀጣይም ወደ ክልልና ወረዳ እንደሚወርድ አስታውቀዋል። በውይይቱ በፋይናንስና ግዥ ስርዓቱ ላይ ያሉ ምቹ አጋጣሚዎች፣ ፈተናዎችና ቀጣይ መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም