የማይጠቅም ምርጫ ለማድረግ መነሳት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ መንግስት ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የማይጠቅም ምርጫ ለማድረግ መነሳት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ መንግስት ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2012 (ኢዜአ) መንግስት ምርጫውን አስመልክቶ የተሻሉ አማራጮችን እየፈለገ ባለበት ወቅት ሕዝብንም ሆነ አገርን የማይጠቅም ምርጫ ለማድረግ መነሳት ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ መንግስት ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በተደረገው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥራት የሚያስችል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ ምርጫ በአንዳንድ ፓርቲዎችና ልሂቃኖች ዘንድ መደረግ የለበትም በተባለ ጊዜ መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ሆኖም በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሺኝ ምክንያት በጊዜው መካሄድ እንደማይቻል በመታወቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ በይፋ መግለጹም ይታወቃል።
በወርርሺኙ ምክንያት ምርጫ ማራዘም ያጋጠመው ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም አገሮች መሆኑ እሙን እንደሆነም አንስተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ከምርጫ ባለፈም ዓለም ዓቀፋዊ ክንውኖችም መሰረዛቸውን የጠቀሱት ዶክተር አብይ ''ኦሊምፒክ ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተራዝሟል፣ የዱባይ 2020 ኤክስፖ በተመሳሳይ ለአንድ ዓመት ተራዝሟል'' ብለዋል።
በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ካሳወቀ በኋላ መንግስት ያሉትን አማራጮች ሲያስጠና መቆየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''በሶስት ቡድን የተደራጁ ሙያተኞች ጥናት አድርገዋል'' ብለዋል።
የጥናቱን ውጤት መነሻ በማድረግም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጠው ለሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መላኩን ተናግረዋል።
''ይህ ጉዳይም የህዝብ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ በመሰንበቱ ከሕግ ባለሙያዎችና ከተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተለያዩ አስትያየቶች እየተሰሙ ይገኛሉ'' ነው ያሉት።
''እየቀረቡ ያሉ አስተያየቶችንም ሕጋዊ ወይም ሕገ-መንግስታዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የሚቀበሉ፣ ሕገ-መንግስታዊ ትርጓሜን የተሻለ አማራጭ አድርገው የሚያቀርቡና ጉዳዩ በፖለቲካ መፍትሄ ቢሰጠው ይሻላል የሚሉ ናቸው'' በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶስት ክፍለው አብራርተዋል።
መንግስት ያቀረባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ መሰል ገንቢ አስተያየቶችና ትችቶችን ያቀረቡ አካላትን አመስግነዋል።
``የሃሳብ ፍጭትና ውይይቶች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ቢሆንም ውይይቶቹ በጠረጴዛ ዙሪያ ከሆነ አገር የሚገነባ ሲሆን ለጥፋት መቀስቀሻ ከዋሉ ግን የስልጣን ጥመኞችን ያፈራሉ'' ብለዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ መስጠቱ የተሻለ ተቀባይነት አግኝቷል ነው ያሉት።
አማራጩ የተሻለ የተባለው የወቅቱን ችግር ብቻ ለማለፍ ሳይሆን ለወደፊትም ሕገ-መንግስታዊነትን ለማጎልበት ይረዳል የሚል እሳቤም ተይዟል።
ጀርመን፣ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ኮሎምቢያ ካናዳን የመሳሰሉ የተሻለ ህገ መንግስት አላቸው የሚባሉ አገሮች በዚህ መንገድ ተጉዘው ክፍተት ሞልተዋል።
የሽግግር መንግስትን የተመለከተው የመፍትሄ አማራጭን የሚያቀርቡ አካላትም ሕገ መንግስቱ ከዚህ ውጪ ሌላ መፍትሄ የሌለው አድረገው ማቅረባቸው ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል።
የቀረበውን ሕገ-መንግስትን የመተርጎም የመፍትሄ ሃሳብ በተመለከተም ሙሉ ስልጣን ያለው የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በመሆኑ መመለስ ያለበትም እሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ሙያተኞች አስተያየት እየሰጡበትና የሌሎች አገራት ልምድ እየተቀመረ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ዐቢይ፤ ''ከዚህ ውጪ ሁሉም ህገ-መንግስት ተርጓሚና የህገ መንግስት ዳኛ ከሆነ ለማንም የማይበጅና ምስቅልቅል አካሄድን የሚያሰከትል ነው'' ብለዋል።
''ከምንም በላይ በዚህ ወቅት የሽግግር መንግስት የሚለው ሃሳብ ከሕግ ብቻ ሳይሆን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለኢትዮጵያ የሚበጅ አይደለም'' ብለዋል።
ወረርሽኙ ለአገር ሉዓላዊነት ስጋት በደቀነበት ሁኔታ የሽግግር መንግስት ይመሰረታል ማለት መቋጫ የሌላው ውይይትም ይባል፣ ድርድር መጀመር ሓላፊነት የጎደለው ሕገ ወጥነት መሆኑን አስምረውበታል።
በመጨረሻም የማይጠቅም ምርጫ ለማድረግ መነሳት አገርንና ሕዝብን ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ነው ያሉት።
ለዚህም በቂ ዝግጅት በመንግስት በኩል መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው ሕዝቡም ነገሩን በጥሞና እንዲከታተል ጠይቀዋል።