ቀጥታ፡

“መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ምርጫው እንዲራዘም ማድረጉ ከህግ አግባብ ውጭ አይደለም" ... አቶ ዛዲግ አብርሃ

 አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2012 (ኢዜአ)“መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ምርጫው እንዲራዘም ማድረጉ ከህግ አግባብ ውጭ እንደሰራ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም” ሲሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኮቪድ 19 እና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት ሚኒስትሩ ምርጫ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ የሚካሄድ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰዎችን መራራቅ የሚጠይቅ በመሆኑ በኢትዮጵያ ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ ሆኗል ይላሉ።

“ይህን አስቸጋሪ ወቅት አልፎ ምርጫ ለማካሄድ የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ተቀባይነት ያለው አሰራር ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የሚያደርሰውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት ለመቀነስ ዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ እንዲራዘም መደረጉም ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።  

"በአሁኑ ወቅት መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምርጫው እንዲራዘም ማድረጉ ከህግ አግባብ ውጭ እንደሰራ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም" ሲሉም አስረድተዋል።

“ዘንድሮ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች በስልጣን ላይ ቢሆኑ ሊወስዱት የሚችሉት እርምጃ ነው የተወሰደው” ብለዋል አቶ ዛዲግ።  

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት በምርጫ መራዘምና የህግ አማራጮች ጥናት ላይ የተሳተፉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው መራዘም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

በመሆኑም ምርጫው ለህዝብና ለአገር ደህንነት ሲባል መራዘሙ ትክክለኛ አማራጭ እንደሆነም አቶ ዛዲግ ተናግረዋል።

ቀውስ በተከሰተባቸው የተለያዩ አገሮች የተካሄዱ ምርጫዎች የገዢ ፖርቲዎችን አሸናፊነት ያረጋገጡ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተከሰተበትና በሽታውን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገበት ወቅት የሚካሄድ ምርጫ የገዢውን ፓርቲ አሸናፊነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ዛዲግ ከዛ ይልቅ መንግስት ምርጫው በትክክለኛው አካሄድ እንዲከናወን እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም