ያለማ መሬትን አልምቶ ለስራ እድል ፈጠራ እንዲውል እየተሰራ ነው.... ርእሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ያለማ መሬትን አልምቶ ለስራ እድል ፈጠራ እንዲውል እየተሰራ ነው.... ርእሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ
ደሴ ኢዜአ ሚያዚያ 28/2012. በአማራ ክልል መልማት ሲገባው ሳይለማ የቆየ መሬትን በመለየት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እንዲውል እየተሰራ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳና ቃሉ ወረዳ በተፋስስ የለማውን አትክልትና ፍራፍሬ ጎብኝተዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መልማት ሲገባው ያልለማ ጦም አዳሪ መሬት ተለይቶ ወደ ልማት እንዲገባ ጥረት እተደረገ ይገኛል።
ይህን ያልለማና ለምነቱ የተሟጠጠ መሬት የአርሶ አደሩን ጉልበት ተጠቅሞ በተፋሰስ በማልማት ለስራ እድል ፈጠራና ለወጣቱ የገቢ ምንጭ አገልግሎት እንዲውል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ደቡብ ወሎ የተፈጥሮ አቀማመጡ አስቸጋሪ ቢሆንም አርሶ አደሩ ተቀናጅቶ ስነ ምህዳርን መሰረት ያደረገ ልማት በማካሄድ ኢኮኖሚያዊ ተጠቀሚነቱን እንዲያረጋግጥ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል ።
በዚህም ቀደም ሲል የለማውን ተፋሰስ በአትክልትና ፍራፍሬ በመሸፈን ለገቢ ምንጭነትና ለኢኮኖሚው መነቃቃት እየተከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ይህ መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋትም እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ከድህነት ለመውጣት እየተከናወነ ያለው ተጨባጭ ስራ በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲደገፍ ይደረጋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው በዞኑ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልሶ እንዲያገግም እየተደረገ ይገኛል።
ቀድሞ ማገገም የቻለውን መሬትም ለ8 ሺህ ወጣቶች በማከፋፈል አልምተው እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።
በተፋሰሶቹ ላይ በልማት ስራ የተሰማሩት ወጣቶች በመንግስትና በባለሙያዎች በተደረገላቸው እገዛ ሃብት በማፍራት ከቤተሰብ ጥገኝነት እንዲላቀቁ ተደርጓል።
የቃሉ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ሁሴን ሚላ በበኩላቸው በወረዳው 700 ሄክታር መሬት በተሰፋሰስ ልማት በአትክልትና ፍራፍሬ ተሸፍኗል።
በአትክልትና ፍራፍሬ እየለማ ካለው መሬትም በዓመት ከ280 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምርቱን ወደ ማዕከላዊ ገበያ አቅርበው እንዲሸጡ የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በቃሉ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አደም እንድሪስ በሰጡት አስተያየት በአንድ ሄክታር መሬት ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካንና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት ከሽያጩ ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል።
በግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላቸው ተከታታይ ድጋፍም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ከሚሰበስቡት ምርት ሽያጭ እስከ 330 ሺህ ብር ድረስ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል ።
በርዕሰ መስተዳደሩ የሚመራው ቡድን ጉብኝት እንደቀጠለ ሲሆን ማምሻቸውንም በቃሉ ወረዳ ደጋን አካባቢ የለማ አትክልትና ፍራፍሬ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።