ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በልማት ስራ ለመደገፍ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዳማ ሰኔ 27/2010 በአዳማ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ያመጡትን ለውጥ ለመደገፍ የልማት ስራና የደም ልገሳ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ። የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ባለሚ በአዳማ ከተማ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት የፕሮግራሙ ዓላማ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሁሉም መስክ እያስመዘገቡ ያሉትን ለውጦችን ለማስቀጠል ያላቸውን ድጋፍና አክብሮት  በልማታዊ ሰራዎች ለመግለጽ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጡትን ለውጥ ለማገዝ" ዴሞክራሲን እናበርታ ለውጥን እንደግፍ "በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ሐምሌ 1/ 2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ለማካሄድ ታቅዶ ነበር። ከዚህ ይልቅ ለውጡን የልማት ሥራዎችን በማከናወን ከጎናቸው መቆም አለብን በሚል ወስነው የድጋፍ ሰልፉን ወደ ጽዳትና የደም ልገሳ ፕሮግራም በመቀየር ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ "በቅርቡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ለማውገዝ፤ በጥቃቱ ህይወታቸው ላለፈው ዜጎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ እና የተጎዱትንም ለማገዝ ጭምር ነው" ብለዋል አቶ ተስፋዬ። በቀጣይነት በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠልና ለውጤት ለማብቃት በአንድነት ለመረባረብ እንደተነሳሱም ገልጸዋል። ቄሮዎች በአንድነት ለውጡን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡ "በሀገር ደረጃ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በውጤታማነት ዘላቂ እንዳይሆን ለማጨናገፍ የሚጥሩ አካላትን በንቃት በመከታተል በጋራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል "ብለዋል። የኮሚቴው አባል አቶ ዳግም ጥበቡ በበኩላቸው የከተማዋ ባለሃብቶች፣ የለውጡ አንቀሳቃሽ ቄሮዎችና ሌሎችም ነዋሪዎች በተቀናጀ መልኩ ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ "ልማት፤ ዴሞክራሲ፤ መደመርና የፍቅር አንድነትን ለመንቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ተግባር ለማክሰም ሁላችንም በተባበረ ክንድ መታገል አለብን "ብለዋል። በሌላ በኩል ኮሚቴው በመጪው አዲሱ ዓመት የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት፤ ፍቅርና ግንኙነትን ለማደስ በራሱ ወጪ 400 ኢትዮጵያውያንን ወደ ኤርትራ ይዞ ለመጓዝ ማቀዱንም አቶ ዳግም ጥበቡ አመልክተዋል፡፡ "አሁን ያገኘነውን  ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ፣ የህዝቦች አንድነትና ሀገራዊ ፍቅር  ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የክልሉ ወጣቶች፣ ቄሮዎችና ሌላውም ህብረተሰቡ በትብብር ይበልጥ ተሳስሮ መስራት አለበት" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ በመጪው እሁድ የሚካሄደው የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎች የተሳካ  እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣው አስተባባሪ ኮሚቴው መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም