የደም ልገሳ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የደም ልገሳ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ገለጹ
ዲላ፣ ሚዛን ሚያዝያ 28/2012 (ኢዜአ) - ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የተቀዛቀዘውን የደም ልገሳ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በጌዴኦ ዞን በጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ገለጹ።
ወጣቶችና አመራሮች የተሳተፉበት የደም ልገሳ ሥነ ሥርዓት ትናንት በዲላ ከተማ ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት ወጣት ብሩክታይት በቀለ ለኢዜአ እንዳለችው እሷን ጨምሮ 14 የሚደርሱ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ደም ልገሳው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ይህም በአሁኑ ወቅት የጤና ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸውን ተከትሎ ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በተለይም እናቶች ለጉዳት እንዳይዳረጉ በማስብ እንደሆነ ወጣት ብሩክታይት ተናግራለች።
ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በተለይም ወላድ እናቶች በደም እጦት ሳቢያ ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደማይገባ የተናገሩት ደግሞ የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ አብርሃም ሆርዶፋ ናቸው።
"በግሌ የምሰጠው ደም የእናቶችን ሕይወት ከሞት የሚታደጋቸው በመሆኑ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው ብለዋል።
በተለይ በዚህ ወቅት በኮሮና ሳቢያ የተቀዛቀዘው የደም ልገሳ ለማስቀጠል ሁሉም አካል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።
የገደብ ከተማ ከንቲባ አቶ ከተማ ሞገስ በበኩላቸው እንደ አመራር በደም ልገሳው የተሳተፉት ለወገን ደራሽነታችንን ለማሳየትና ለሌሎች ዓርአያ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሽፈራው "ደም በመለገስ የሰውን ሕይወት ለማትረፍ መሳተፍ የተለየ ስሜት አለው" ብለዋል።
የዲላ ደም ባንክ አስተባባሪ ሲስተር መስታወት ዘውዴ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በዞኑ በወር ከሚታቀደው 183 ዩኒት ደም ውስጥ በአማካይ ከ90 በመቶ በላይ ይሰበሰብ የነበረው ከኮሮና ሥጋት ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ከ10 በመቶ ያነሰ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የቤንች ሸኮ ዞን የብልጽግና ፓርቲና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ አመራሮች ደም ለግሰዋል።
የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ምናሴ እንደገለፁት ደም መለገስ የሰው ልጅ ሕይወት ማስቀጠል በመሆኑ ታላቅ ሰብአዊ ተግባር ነው።
በዞኑ የሚገኙ የፓርቲው አባላት ደም እንዲለግሱም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዞኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደነቀ ደሳለኝ በበኩላቸው "ሰው በማዳን በሚደረግ ተግባር ያለ ልዩነት ሁሉም ርብርብ ማድረግ አለበት" ብለዋል።
ፓርቲው የሕዝብ ደህንነትን በማስቀደም ወረሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።