የኮካ ኮላ ፋውንዴሽን ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኮካ ኮላ ፋውንዴሽን ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2012 (ኢዜአ) የኮካ ኮላ ፋውንዴሽን ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚውል ነው።
የኮካ ኮላ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ የህግ፣ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉስ አለሙ፤ ድርጅቱ የኮቪድ-19ን ለመከላከልና የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በተለይ በተለያዩ አገራት በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶችና ማህበራት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ወረርሽኙን ለመከላከልና የሚያደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ለመቀነስ እንዲቻል የበኩሉን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ድርጅቱ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ችግር እስኪወገድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጸሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋአረጋ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከ22 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ከግንዛቤ ጀምሮ በ134 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ በሚገኝባቸው ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
በዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት መረጃ መሰረት በኮቪድ-19 ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጿል።
በዚህም ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
በመሆኑም የዚህ ወረርሽኝ ተግዳሮት ከፍተኛ አንደመሆኑ ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከግል ሴክተሩ ጋር በመደጋገፍ ይህንን ወቅት ማለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ድርጅቱ አሁን ያደረገው ድጋፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከአሁን ቀደም እርዳታ ለሚሹ በተለይም ለምግብ አገልግሎት፣ በጎዳና ላይ ለሚገኙ ህጻናቶች፣ ሴቶች እና አረጋውያንን የሚውል የ3 ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ ማደረጉን አስታውሰዋል።
ማህበሩ ይህንንም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የማከፋፈል ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በቀጣይም እጥረት ባለባቸውና ሰፊ ድጋፍ ለሚሹ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች እንደሚውል ገልጸው ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አሁን ላይ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አባላትና ከ250 ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች አሉት።