በኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ተደስተናል... የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፓርት ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ተደስተናል... የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፓርት ተሳታፊዎች
መቀሌ ሰኔ 27/2010 የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዳስደሰታቸው በመቀሌ እየተካሄደ ባለው ዘጠነኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፓርት ልኡካን ቡድን አባላት ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የስፖርት ልኡካን ቡድን አባላቱ የመቀሌ ህዝብ ያደረገላቸው አቀባበል የኢትዮጵያዊያን ለእንግዳ ያላቸውን ከበሬታ ያሳያል ብለዋል፡፡ በናይጄሪያ ሌጎስ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ዳይሬክተር ዶክተር ጆሴፍ አወይንፋ በመቀሌ ከተማ ህዝብ ለተደረገላቸው አቀባበል መስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ከአሉላአባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ጀምሮ እስከ ማረፊያቸው ድረስ በህዝቡ የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ እንዳስደሰታቸውም ነው የገለጹት፡፡ ዶክተር ጆሴፍ እንዳሉት በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድር አፍሪካውያን ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ከኡጋንዳ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌደሬሽን ዋና ፀሐፊ የተወከሉት ሚስ ፔኒናህ ካቤንግ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና የሚሰጠው አክብሮት የሚያኮራ ባህል ነው" ብለዋል። የእንግዳ ተቀባይነቱ ባህል ለሌሎች በአርአያነት የሚታይ መሆኑን ገልጸው የስፖርት ውድድሩ በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ትስስር በተለያየ መንገድ እንዲጠናከር የሚያደርግ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አፍሪካውያን ባህላቸውና ልምዳቸውን የሚጋሩበት አንዱ መንገድ የስፖርታዊ ውድድሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከቦትስዋና ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት ሚስተር ሞሬሲከ ኢትሲንግ ናቸው፡፡