ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ ለተጀመረው አገራዊ መግባባትና ሰላም የበኩሉን እንዲያበረክት ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 ህዝበ ሙስሊሙ የእርስ በእርስ አንድነቱን አጠናክሮ ለተጀመረው አገራዊ መግባባትና ሰላም የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። ምክር ቤቱ ዛሬ ''የኢትዮጵያ ሙስሊም ሊቃውንት የሰላምና የፍቅር ጉባዔ'' በሚል ስያሜ የሙስሊሙን ህብረተሰብ አንድነት ለማጠናከርና አሁን በአገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍ ያለመ ጉበዔ አካሄደዋል። ከዚህ በፊት 'በድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ' ውስጥ ተይዘው ዓመታትን በእስር ቤት ያሳለፉ “የሙስልም መፍትሄ አፈላለጊ ኮሚቴ'' አባላት በኮንፍረንሱ ላይ ተግኝተዋል። የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሃመድ-አሚን ጀማል በዚህ ወቅት እንዳሉት በሳለፍናቸው የቅርብ ዓመታት በአገር ደረጃ ባጋጠሙት የሰላም አጦት የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ተጎድቷል። በጎሳና በዘር ተከፋፍሎ መጠቃቃትና የዜጎች ከቤት ንበረታቸው መፈናቀል መበራከቱንም ገልጸዋል። አሁን በአዲሱ አመራር በአገሪቱ የቀየሰው የአንድነትና የፍቅር መንገድ በሃይማኖትም በሌላም መመዘኛ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባ በጎ ስራ ነው ብለዋል። በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በዘርና በሃይማኖት ሳይከፋፈል በጋራ ለውጥን በመደገፍ አገራዊ አንድነት ሊያጠናክር ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል። ለዚህም በሙስሊም ህብረተሰብ መካከል ያለው መቃቃር መወገድ ስለሚገባ የሃይማኖት አባቶች እምነትን ሲያስተምሩ ሚዛናዊነትንና መቻቻልን እያስተማሩ አንድነትን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገራዊና ሃይማኖታዊ አንድነት ለማምጣት በሁሉም መስክ ተባብሮ መንቀሳቀስ ሌላ አማራጭ ያሌለው ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል። ከነዚህ መካከል የተቋቋመው የአዲሱ ኮሚቴ አባላት ኡስታዝ አቡበከር አህመድና ሃጂ ኡመር እድሪስ እንዳሉት በመካከላችን ችግር ሲፈጠር መቀራረብና መወያየት የሃይማኖቱም ዋና አስተምህሮ ነው። በመሆኑም አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ሆነ ሙስሊሙን ህብረተሰብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም