የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የቤት ለቤት ልየታ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የቤት ለቤት ልየታ ስራ ጀመረ
ሐረር ሚያዚያ 28/2012(ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የቤት ለቤት ልየታ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የቤት ለቤት ልየታ ስራውን የጀመረው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያ ወረዳ ውስጥ ነው።
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችና አስተዳደር ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን አልይ ስራው ትናንት በተጀመረበት ወቅት እንደገለጹት ተቋሙ ቫይረሱን ለመከላከል ሳኒታይዘር የማምረት፣የለይቶ ማቆያና የናሙና መመርመሪያ የላብራቶሪ ማዕከላትን በማቋቋም አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል።
አሁን ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የሚገኙትን የዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ተማሪዎችን በማስተባበር ቫይረሱን ለመከላከል የቤት ለቤት ልየታ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የቤት ለቤት ልየታ ስራ ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፋና እንዲከላከል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ ስላለው ማህበረሰቡም ለተማሪዎቹ አስፈላጊውን ትበብር እንዲያደርጉ ፕሮፌሰር ጄይላን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ግብረ ኃይል አባል ዶክተር መሐመድ አህመድ በበኩላቸው ባለፉት ወራት በአካባቢው የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማሰልጠን የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አውስተዋል።
የቤት ለቤት ልየታው የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር በሐረማያ ወረዳ በሚገኙ 38 ቀበሌዎች ይከናወናል ብለዋል።
ለዚህም 158 የጤና እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች የሁለት ቀን ስልጠና መውሰዳቸውን እና በቆይታቸውም ከ64ሺ በላይ ቤቶችን በመሸፈን የሰዎችን የሙቀት ልኬት ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከሶማሊያ፣ጅቡቲ እና አረብ ሀገራት መጥተው ሳይታወቁ ከህብረተሰቡ ጋር የተቀላቀሉ ካሉም የቤት ለቤት ልየታው ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የቫይረሱ መከላከል ግብረ ኃይል ፀሐፊ አቶ መሀመዲን ከቢር-ሁሴን እንዳሉት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከዞኑ ግብረ ሃይል ጋር በመተባበር ቫይረሱን ለመከላከል ድጋፍ እያደረገ ነው።
ከድጋፉ ውስጥም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማስተባበር የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫና የተጀመረው የልየታ ስራን ጠቅሰዋል።
በዞኑ በየደረጃው ባለው የአስተዳደር መዋቅር አማካኝነት የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫና ልየታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።
በስራው ከተሰማሩት መካከል የአራተኛ ዓመት የጤና ተማሪ ነዲ ኢብራሂም በሰጠው አስተያየት የቤት ለቤት ልየታ ስራው ቫይረሱ ሳይዛመት ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግሯል።
"እኛም በአሁኑ ወቅት ጊዜያችንን በከንቱ ከምናሳልፍ እራሳችንን ከቫይረሱ እየተከላከልን በዚህ በጎ ስራ ላይ ተሰማርተን እንገኛለን " ብሏል።
በሐረማያ ከተማ የባቴ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሔለን ወንድሙ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባሰማራቸው ተማሪዎች ስለኮሮና መተላለፊያ መንገድና መከላከያው የሰጧቸውን ትምህርት በመተግበር እራሳቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።