ቀጥታ፡

ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ የምግብ እህልና ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ

ደሴ (ኢዜአ) ሚያዚያ 28/2012 በደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደር የሚካሄደውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዳ 100 ኩንታል የምግብ እህልና አራት ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ።

የምግብ እህሉ ድጋፍ ያደረጉት ከኡዝታዝ አቡቦክር አህመድ ሲሆን ተሽከርካሪዎቹ ደግሞ በባለሃብቶች የተሰጠና ለኮሮና መከላከል ስራ በጊዜያዊነት የሚውሉ ናቸው።

የኡዝታዝ አቡቦክር አህመድ ተወካይ ሸህ ሐሰን ሃሚዲን ድጋፉን በሰጡበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም ኡዝታዝ አቡቦክር 100 ኩንታል ዱቄትና ማካሮኒ  ከአዲስ  አበባ በመላክ ለደሴ ከተማና ደቡብ ወሎ ዞን አስረክበዋል።

በጎ አድራጊው  በወሎና ሌሎች አካባቢዎችም ምግብ እህልና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡

ከባለሀብቶቹ መካከል ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ በበኩላቸው ኮሮናን  ለመከላከል በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ከሌሎች ድጋፎች በተጨማሪ "አባዱላ" ተሽከርካሪያቸውን  መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ   አቶ አበበ ገብረመስቀል ድጋፍ ላደረጉት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል እንዲረዳ በደቡብ ወሎ  24 ወረዳዎች ከሁለት ሺህ 700 ኩንታል በላይ የተለያየ የምግብ እህል ከበጎ አድራጊዎች መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ሰይድ መሃመድ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም አራት ባለሃብቶችም በጊዜያዊነት አራት ተሸከርካሪዎቻቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው እነዚህም ደም ለመሰብሰብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ኮሮናን ከመከላከሉ በተጓዳኝ ያጋጠመውን የደም እጥረት ለማሟላተ ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻ በቅርቡ መጀመሩም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም