በትግራይ ኮሮናን ለመከላከል የተጠናከረ የጤና ምርመራና ቁጥጥር ስራ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ኮሮናን ለመከላከል የተጠናከረ የጤና ምርመራና ቁጥጥር ስራ እያካሄደ ነው
መቀሌ ኢዜአ ሚያዝያ 27/12 ዓ/ም--በትግራይ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመከላከል የተጠናከረ የጤና ምርመራ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊና የኮሮና መከላከል ንኡስ ግብረ ኃይል የጤና ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር ርእየ ኢሳያስ እንደገለጹት ፣ ወደ ክልሉ ሰዎች የሚተላለፉባቸው 42 የመግቢያ በሮች ተለይቷል።
በእነዚህ በሮች የቫይረሱ ስርጭት አስቀድሞ ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች መድበው የተጠናከረ የጤና ምርመራ፣የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በክልሉ በተካሄዱ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ሰባት ሺህ 272 ሰዎች ወደ ተዘጋጁ 29 የማቆያ ማዕከላት ገብተው ከመካከላቸውም ሦስት ሺህ ሰዎች የመቆያ ጊዜያቸውን አጠናቀው መውጣታቸውን ዶክተር ርእየ አስረድተዋል።
በአስገዳጅ የማቆያ ማዕከላት የነበሩ 523 ሰዎችም ደግሞ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ተረጋግጧል ብለዋል።
ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻልም በክልሉ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች መካከል 2ሺህ 600 የሚሆኑት ቫይረሱን አስመልክቶ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠና ተሰጥቷዋቸው ወደ መከላከል ስራው መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
በተጓዳኝም ቫይረሱን በጤና ምርመራ ለማረጋገጥ የሚረዱ የላባላቶሪ ማዕከላት በመቀሌ እና ዓዲግራት ከተሞች ተቋቁመው በቁሳቁሶች እንዲሟሉ ተደርጓል ብለዋል።
በአክሱምና ማይጨው ከተሞች ከተማ ተጨማሪ የላባላቶሪ ማዕከል ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለሃብቶች፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለቫይረሱ መከላከያ የሚያግዙ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምናና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለክልሉ ጤና ቢሮ ማበርከታቸውንም ዶክተር ርእየ ጠቁመዋል።
ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የቫይረሱ ምልክቶችና የመከላከያ ዘዴዎችን አስመልክቶ የገጽ በገጽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱንም አመልክተዋል።